የትግራይ ክልል የተስፋ ጉዞ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ክልል የተስፋ ጉዞ
የትግራይ ክልል የተስፋ ጉዞ - የባለአደራ አስተዳደር እና የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ
ህገወጡ የህወሐት ቡድን በስልጣን ጥም፣ በኃይል እርምጃዎች እና በማን አለብኝነት በሚፈጽማችው ድርጊቶች ምክንያት በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሰው ውድመት እና ስቃይ እጅግ ከባድና በታሪክ በጥቁር ጠባሳ ተመዝግቦ የሚዘከር ነው።
ቡድኑ የፖለቲካ ፍላጎቱና የስልጣን ጥሙን ለማርካት ሲል ብቻ የወጣቶች ህይወት ተቀጥፏል፤ ዜጎች ክብራቸውን አጥተው ተሰደዋል። ብዙዎችም አካል ጎዶሎ ሆነዋል። ቤተሰቦች የልጆቻቸውንና የወገኖቻቸውን ህይወት በማጣታቸው ከባድ የሥነ ልቦና እና የማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ወድቀዋል።
የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ እና መፈናቀል አጋጥሟል፡፡ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡
በሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ተሳትፎ እና የፌዴራል መንግስት በወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ መሰረት ህገ ወጥ ቡድኑ ከተወገደ በኋላ በክልሉ መደበኛ የመንግሥት አገልግሎቶችንና መልሶ ግንባታ ስራዎችን ለማስጀመር፣ ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ፣ ህዝቡን ወደ ልማት እንዲመለስ እና ሌሎች ዓበይት የለውጥ ተግባራት እንዲከወኑ ለማስቻል ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር መቋቋሙ ይታወቃል፡፡
ባለአደራ አስተዳደሩ ስራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመሰረተ ልማት እድሳት፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችን መልሶ በመዘርጋት፣ የፈረሱ የመንግስት መዋቅሮች መልሶ በማዋቀር፣ በሰብዓዊ ድጋፍ ማደራጀት፣ ገበያን በማረጋጋት እና በሌሎች መሰል ስራዎች በኩል እያከናወናቸው ያሉ ዓበይት ተግባራት የማህበረሰቡን ተስፋ ያለመለሙ ናቸው።
በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቋረጡ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የባንክና የትራንስፖርት መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሳቸው የሕዝቡን ስቃይ እንዲቀንስ አድርጓል፤ አዲስ ተስፋም አሰንቀዋል።
በህዝብ ተሳትፎ ክልሉን ወደ አስተማማኝ የሰላም እና የመረጋጋት ቀጣና ለመቀየር ህዝባዊ ውይይቶች እየተካሄዱ ናቸው። የመንግስት መዋቅር መልሶ ለመዘርጋት በየደረጃው ያሉ የቢሮ፣ የኤጀንሲ እና የተቋማት ጊዜያዊ አስተባባሪዎችና ኃላፊዎች ምደባ ተከናውኗል፡፡
በህዝብ ፍላጎት መሰረት የታችኛውን መዋቅር የሚመሩ ጊዜያዊ መሪዎች እና አስተባባሪዎችም ተመርጠው መደበኛ ስራዎችን ማሳለጥ ተጀምሯል፡፡
ባለፈው ሳምንትም የፌዴራል ባለአደራ አስተዳደር አዲስ ከተሾሙ የቢሮ ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች ጋር በመወያየት በአጭር ጊዜና በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚከናወኑ ተግባራትን ለይተዋል፡፡
በተለይም የህግ የበላይነትና አሰራርን መዘርጋት፣ ፀጥታን ማረጋገጥ፣ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ መክፈል፣ ንግድን ማጠናከርና ገበያን ማረጋጋት፣ የትራንስፖርትና ፋይናንስ እንቅስቃሴ ማስጀመር፣ እርዳታ ማዳረስ እና የመድሃኒት አቅርቦት ማጠናከር የመሳሰሉ ጊዜ የማይሰጡ ጉዳዮች ላይ በቅድሚያ እንዲተገበሩ በውይይቱ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
ይህንን አስመልክቶ የስድስት ወር መሪ ፕላን መዘጋጀቱና ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው መለየታቸውን፣ የፌዴራል መንግስትና ተቋማት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉም የአስተዳደርና የህዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ አቶ አሰፋ አብርሃ ውይይቱ በተካሄደበት ወቅት አጽንኦት የሰጡት ጉዳይ ነው።
በትግራይ ክልል ያጋጠሙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳቶችን በማቃለል እና መልሶ በማቋቋም ስኬታማ እንዲሆን ህዝቡን በቀጥታ ማሳተፍ፣ ግልጽነት ያለው አሰራር መከተል እና የአካባቢውን ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ሁኔታ ያገናዘበ እቅድ ሲተገበርና ትብብር ሲኖር መሆኑን የሚመለከታቸው አካላት ይገልጻሉ።
የተመደቡት ጊዜያዊ አስተባባሪዎች የተቋማቱን በጀት፣ ንብረት እና የሰው ኃይል በበላይነት በመምራት መደበኛውን የአስተዳደር አወቃቀር መልሶ ለመዘርጋት እና የስድስት ወራት እቅድ በማዘጋጀት በጋራና በትብብር እንደሚሰሩም በተካሄዱ ውይይቶች ላይ አረጋግጠዋል፡፡
የተጀመሩ ሁለንተናዊ እና አርቆ አሳቢ እርምጃዎች ክልሉን ወደ ሙሉ መረጋጋትና ዘላቂ ልማት ለማሸጋገር ጠንካራ መሰረት እንደሚጥሉ ታምኖበታል፡፡
የባለአደራ አስተዳደሩ አሁናዊ እንቅስቃሴና ተግባር ሲለካ በተሰጠው ተልዕኮና በፅኑ መርህ መሰረት የህዝቡን ስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ቁስል በማከም ተስፋ ለማደስ፣ የክልሉን መልሶ ግንባታ ለማፋጠን ብሎም ሁለንተናዊ የክልሉን አዲስ ምዕራፍና የለውጥ ጉዞ መጀመሩን ያሳያል፡፡
ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህዳሴ እውን እንዲሆን ፍትሃዊና አካታች እድገት ለማስቀጠል መንግስት ትኩረት እንደሰጠውም ያመላክታል፡፡
አሁን በህዝቡ የአስተዳደር፣ የመንግስት አገልግሎት እና የፀጥታ ጥያቄዎች ላይ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አዲስ የተመረጡ መሪዎችን ወደ ቀበሌ መዋቅሮች በማውረድ ስራ እንዲጀምሩ የማድረግ እና የተሻለ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን የመስራት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በዚህ ወሳኝ ወቅት የተቋቋመው የትግራይ አደራ አስተዳደር የተደራረበውን የህዝብ ችግር በቅደም ተከተል በማስቀመጥ፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ መሰረት ለመጣል ባልተቋረጠ ጥረት ስራ ላይ ይገኛል።
የትግራይን ህዝብ የራቀውን ሰላም እንዲጎናጸፍ ይፈልጋል፤ መለወጥ፣ ማደግ፣ መበልጸግ ይሻል፤ ላለፉት በርካታ ዓመታት ያጣቸውን የልማት ትሩፋቶች ማጣጣም አለበት፡፡
በክልሉ ቱሪዝም፣ የማዕድንና ሌሎቸን ጨምሮ ያሉትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ ወደ ሀብት መቀየር ያስፈልጋል። ትግራይን መልሶ መገንባት፣ ሌሎች ክልሎች የደረሱበት እድገትና ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ እንድትደርስ የሁሉም የባለድርሻ አካላት ትብብርና በጊዜ የለንም መንፈስ መስራት ወሳኝ ጉዳይ ነው።