የኢትዮጵያ አስቻይ የንግድና ኢንቨስትመንት የፖሊሲ እርምጃ ለአልሚ ባለሃብቶች ምቹ ምኅዳር ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አስቻይ የንግድና ኢንቨስትመንት የፖሊሲ እርምጃ ለአልሚ ባለሃብቶች ምቹ ምኅዳር ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 23/2019(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አስቻይ የንግድና ኢንቨስትመንት የፖሊሲ እርምጃ ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አልሚ ባለሃብቶች ምቹ ምኅዳር መፍጠሩን የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሴቶች ቢዝነስ ምክር ቤት ገለጸ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
የመደመር መንግሥት የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ፍኖት የማድረግ ትልም በሁሉም መስክ እመርታዊ ውጤቶችን ማስገኘቱን ቀጥሏል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብርም የኢትዮጵያን የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና የዲጂታል ዘርፍ ንግድና ኢንቨስትመንት በማበረታታት ጸጋን ወደ ጥቅም ቀይሯል።
ይህም የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ በማስፋት የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አልሚዎችን ንቁ ተሳትፎ እያጎለበተ ይገኛል።
የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርም በሁሉም ዘርፍ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት አቅም ፈጥሯል።
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሴቶች ቢዝነስ ምክር ቤት ሊቀመንበር አይሻ መሐመድ ሰኢድ አል ሙላ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሀገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ዕድገትም በሀገራቱ መንግሥታት ጠንካራ ትብብር የተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት አስቻይ የፖሊሲ እርምጃም ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አልሚ ባለሃብቶች ምቹ ምኅዳር መፍጠሩን ተናግረዋል።
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሴት አልሚዎችም በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩበትን ትልቅ መሰረት መጣሉን አንስተዋል።
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሴቶች ቢዝነስ ምክር ቤትም በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች መሳተፍ የሚያስችሉ ጉዳዮችን እየለየ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በቀጣይም በግብርና፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በግብርና ማቀነባበርና በሌሎች በርካታ የንግድና የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሳተፍና የንግድ ትስስርን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
"አዲስ አጋርነትን ማጠናከር እና የወደፊቱን አብሮ መምራት" በሚል መሪ ሃሳብ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና የኢትዮጵያ የንግድ ልዑካን የ2026 የንግድ ፎረም ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል።