ቀጥታ፡

5ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የማህበረሰብ ጤና ጉባኤ በአዲስ አበባ ለማስተናገድ አስፈላጊ ዝግጅት እየተደረገ ነው- ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 23/2019(ኢዜአ)፦አምስተኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የማህበረሰብ ጤና ጉባኤ በአዲስ አበባ ለማስተናገድ አስፈላጊ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ አስታወቁ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን አምስተኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የማህበረሰብ ጤና ጉባኤ ዝግጅት አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል።


 

በመግለጫቸውም፤ በጤና ሚኒስቴርና በአፍሪካ የጤና መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል (African-CDC) ትብብር የተዘጋጀው 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የማህበረሰብ ጤና ጉባኤ ከኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት፣ አፍሪካ የጤና መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል (African-CDC) እና ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗ ጉባኤውን ለማስተናገድ ዕድሉ እንደተሰጣት ተናግረዋል።

ጉባኤዉም ''የአፍሪካ ጤና ደህንነትና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና የመቋቋም አቅም መሸጋገር'' በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም ጉባኤውን በስኬት በማስተናገድ በጤና ዘርፍ የተገኙ ልምድና ተሞክሮዎችን ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለማሳየት እንደምትጠቀምበት አንስተዋል።

የጉባኤው ዋና መሪ ሃሳብ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ በአፍሪካ የጤና ራስን መቻል፣ የጤና ሥርዓት ጥንካሬና የወረርሽኝ መከላከል አቅምን ማሳደግ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።

አፍሪካ በጤና ዘርፍ የራሷን አቅም በማጠናከር፣ በሳይንሳዊ ምርምር፣ በቴክኖሎጂና በአህጉራዊ ትብብር የጤና ችግሮቿን በራሷ ለመፍታት የሚያስችላትን አቅም ማዳበር እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

በጉባኤው የሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ሙያተኞች፣ የግሉ ዘርፍና የልማት አጋሮች በአፍሪካ ጤና አጀንዳዎች ላይ የጋራ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሲዲሲ በአህጉሪቱ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም የአፍሪካን የጤና አጀንዳ በዓለም አቀፍ መድረኮች በጋራ በማቅረብ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።


 

ጉባኤው የጤና ዘርፍ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ፣ የጤና መሠረተ ልማትን ለማጠናከር፣ የድንገተኛ ጤና አደጋ ምላሽ አቅምን ለማሳደግና ሳይንሳዊ ምርምርና ዲጂታል ጤናን ለማስፋፋት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በአፍሪካ የመድኃኒትና የሕክምና ቴክኖሎጂ ምርት፣ የጤና ኢንቨስትመንትንና በአህጉሪቱ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን ክህሎት ማሳደግ በጉባኤው የሚመከርባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በጉባኤውም እስከ አሁን ድረስ ከ29 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ለመታደም መመዝገባቸውንና ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች እንደሚጠበቁ ገልጸዋል።

ከእነዚህም 18 ሺህ በላይ የሚሆኑት ተሳታፊዎች የእውቅና ሰርተፊኬት አግኝተው የመግቢያ ሂደታቸውን ማጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ለአገር ውስጥ ተሳታፊዎች ተጨማሪ የምዝገባ እድሎች እንደሚከፈቱ አስታውቀዋል።

የጉባኤው ዝግጅት ከጤና ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ከትራንስፖርት፣ ከሎጂስቲክስ፣ ከደኅንነት፣ ከቱሪዝምና ከሌሎች ዘርፎች ጋር በተቀናጀ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጉባኤው ዝግጅት እስከ መጨረሻው የማስተናገድ ሂደት መድረሱን ገልፀዉ፤ የቪዛ፣ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ዝግጅቶችም እየተጠናቀቁ መሆኑን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም