ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የተመዘገቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስኬቶችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር በተግባር እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2019 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የተመዘገቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስኬቶችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል እቅድ ወጥቶ በመተግበር ላይ መሆኑን የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ በመግለጫቸው፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሁለንተናዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት በቁጭትና በጊዜ የለኝም መንፈስ እቅዶችን አውጥቶ ሲተገበር ቆይቷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበር በኢኮኖሚ እና በተለያዩ የልማት ዘርፎች ራስን መቻል ላይ ያተኮረ ስልታዊ ዕቅድ ይፋ አድርጎ እየተገበረ ይገኛል ብለዋል።

ይህ ዕቅድ ክልሉ ያለውን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ የመሬት ለምነትና የሰው ኃይል በመጠቀም የውጭ እርዳታና ጥገኝነትን ማስቀረት እንዲሁም የኑሮ ውድነትን መቀነስ እንደ ዋና ዓላማ አድርጎ የያዘ ነው።

በተለያዩ ደረጃዎች ሰፊና ጥልቅ ውይይት የተደረገበት ይህ የአምስት ዓመቱ ስልታዊ ዕቅድም ወደ ሙሉ ትግበራ መግባቱን አቶ ሃይሉ አመልክተዋል።

በዕቅዱ የተቀመጡ ዋና ዋና ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ አምስት ዋና ዋና የልማት ሞተሮችን ለይቶ ወደ ሥራ መገባቱንም አስታውሰዋል።

እነዚህም የሰው ኃይል ክህሎትን ማሳደግና የሥራ ፈጠራን ማበረታታት፣ ማሽነሪና ቴክኖሎጂን ማስፋፋት፣ ገቢን በማሳደግ የፋይናንስ አቅርቦትን ማጠናከር፣ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ማሳደግ፣ እንዲሁም ሞዴል የገጠር መንደርና ከተሜነትን ማረጋገጥ ናቸው ብለዋል።

የዕቅዱ ዋና ዓላማ ሁሉንም ተግባራት በመደመር አስተሳሰብ በመምራት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር መሆኑን የገለጹት አቶ ሃይሉ፣ ይህንንም ዓላማ ከእቅድ በላይ ለማሳካት ሰፊ ውይይት ተካሂዶ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

ይህንንም ለማሳካት ኢኮኖሚን ማጠናከር፣ ማኅበራዊ ልማትን መምራትና የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ዕቅዱን ለማሳካት በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች፣ ከመንግሥት ሠራተኞችና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑንና የጋራ መግባባት መፈጠሩንም አመልክተዋል።

በዚህም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ክልሉን ወደ ከፍተኛ የለውጥ ጉዞ ለማሸጋገር በተግባር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም