የመደመር መንግሥት ወጣቶች በሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው - ከንቲባ አብዱላሂ አደም - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት ወጣቶች በሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው - ከንቲባ አብዱላሂ አደም
ድሬደዋ፣ ጥቅምት 23/2019(ኢዜአ)፡-የመደመር መንግሥት ወጣቶች በሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደም ተናገሩ።
አስተዳደሩ "የዛሬ ወጣት፣ የነገ የድሬዳዋና የኢትዮጵያ ተስፋ" በሚል መሪ ሐሳብ ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ዛሬ የውይይት መድረክ አካሄዷል።
ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደም በወቅቱ እንዳሉት፣ የመደመር መንግሥት ወጣቶች በሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው።
በዚህም በማኅበራዊ፣ በምጣኔ ሀብታዊና በፖለቲካው ዘርፎች የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት በተጨባጭ እመርታ እየተጓዘ መሆኑን አንስተዋል።
አዲሱ የድሬዳዋ አስተዳደር የተጀመሩትን ጥረቶች ይበልጥ ፍሬያማ ለማድረግ ከገጠርና ከከተማ ወጣቶች ጋር የቀረበ ትስስር በመፍጠር የተሻለ ውጤታማ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አብዱልጀዋድ መሐመድ በበኩላቸው፣ ወጣቶች ለሰላም፣ ለልማትና ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል።
የመደመር መንግሥት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ እያሳደገና አገር ገንቢነታቸውን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
በየደረጃው የሚገኘው ወጣት የእርስ በርስ ትስስርንና አንድነቱን በማጠናከር ለአገር ከፍታና ብልጽግና እያከናወነ የሚገኘው የበጎ ፈቃድ ልማት መጠናከር እንዳለበት የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ ናቸው።
ለዚህም አስፈላጊው አሠራርና አደረጃጀት ተዘርግቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን አስታውሰው ወጣቶች ጤናማ ዜጎች ሆነው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በየወረዳው ዘመናዊ የስፖርት ሜዳዎችና ማዕከላት መስፋፋታቸውን አንስተዋል።
በውይይቱ ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል ወጣት ደሃቦ አደምና ወጣት አሸናፊ ስዩም፣ የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅና በክረምትም ሆነ በበጋ በሚካሄዱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ወጣቱ በየወረዳቸው በሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ ለድሬዳዋ ዕድገት ኃላፊነቱን በተሻለ ደረጃ እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።