የአፍሪካ የለውጥ ብርሃን፤ የላቀ የዲፕሎማሲ ማዕከል- አዲስ አበባ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የለውጥ ብርሃን፤ የላቀ የዲፕሎማሲ ማዕከል- አዲስ አበባ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2019(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ የለውጥ ብርሃን፤ የላቀ የዲፕሎማሲ ማዕከል- አዲስ አበባ
በሚፍታ ሽፈራ
ከተማ የሰዎች የኑሮ ማዕከል፣ የታሪክና የባህል መገለጫ፣ የማኅበራዊ ግንኙነትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መድረክ ነው። የከተማ ልማትም የሚለካው በነዋሪዎች የኑሮ ጥራት፣ በሚፈጥረው የኢኮኖሚ ዕድል፣ በሚጠብቀው ታሪካዊ ማንነትና በሚያጠናክረው ማኅበራዊ ትስስር ጭምር ነው። ይህንን እውነታ በተግባር እያሳዩ ካሉ ጥቂት የዓለም ከተሞች መካከል አዲስ አበባ አንዷ ናት።
በቀደሙት ዓመታት አዲስ አበባ ከስሟ፣ ከታሪካዊ ክብሯና ከነዋሪዎቿ የኑሮ ፍላጎት ጋር የማይጣጣሙ በርካታ ችግሮች ይታዩባት ነበር። የአካባቢ ብክለት፣ የአረንጓዴ ስፍራ እጥረት፣ የወንዝ ዳርቻዎች መበከልና የመንገድ መጨናነቅ ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል ነበሩ።
ከለውጡ በኋላ በገበታ ለሸገር የተጀመረውና በኋላም ወደ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ የተስፋፋው የልማት አቅጣጫ የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር አዲስ መነሳሳት ፈጥሯል። የዚህ ለውጥ መሠረት ከመደመር እሳቤ ጋር ይገናኛል። መደመር የተለያዩ ሀብቶችን፣ አቅሞችን፣ ባህሎችንና ፍላጎቶችን በማቀናጀት ለጋራ ጥቅም ማዋል ነው። በዚህ እሳቤ ልማት የሰውን ክብር የሚያስጠብቅ፣ ሁሉንም የሚያሳትፍና ለጋራ ተጠቃሚነት የሚያበቃ ነው።
በዚህ አቅጣጫ ከተከናወኑት የልማት ሥራዎች መካከል የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ይጠቀሳሉ። የኮሪደር ልማት መንገዶችን ከማስፋትና ከማስዋብ ባለፈ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን፣ የአረንጓዴ ስፍራዎችን፣ የመዝናኛ ማዕከላትንና የንግድ ቦታዎችን በአንድ ላይ ማቀናጀት የቻለ ነው ። ይህም የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የነዋሪዎችን፣የንግድ እንቅስቃሴና የማኅበራዊ ተግባቦት ዕድል አሳድጓል።
በተመሳሳይ የወንዝ ዳርቻ ልማት የተፈጥሮ ሀብትን ከሕዝብ ጥቅም ጋር የሚያቀናጅ ግዙፍ የልማት ሥራ ነው። የተበከሉና በተለያዩ ችግሮች የተጎዱ የወንዝ ዳርቻዎችን ወደ አረንጓዴ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የስፖርት ማዕከላት፣ የንግድና የቱሪዝም መዳረሻዎች የመቀየር ጥረት የአካባቢ ጥበቃንና የማኅበራዊ ጥቅምን አብሮ አስተሳስሯል።
መዲናዋን እየቀየሩ ያሉ ሁለገብ የልማት ሥራዎች የመደመር የእይታ አድማስ በተግባር ያሳዩ ናቸው። የተለያየ አቅም፣ እውቀትና ሀብት በማቀናጀት የተከናወኑት እነዚህ ሥራዎች፤ የከተማዋን ነባር ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ከዘመናዊ ግንባታ ጋር በማስማማት ዘላቂ የልማት ውጤት እንዲመዘገብ አስችለዋል።
የዘመናዊ መሠረተ ልማቶች መዘርጋት፣ የትራፊክና የመንገድ መጨናነቅ መቃለል እንዲሁም የዲጂታልና የተቀናጁ አገልግሎቶች መስፋፋት የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና የኑሮ ዘይቤ ፈጣንና ቀልጣፋ አድርጎታል።
የተዋቡ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ የወንዝ ዳርቻ መዝናኛዎች፣ እና የታደሱ ታሪካዊ ቅርሶች አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ያላቸው የኮንፈረንስና የዕረፍት ጊዜ መዳረሻዎች አድርገዋታል። ይህም የቱሪዝም ፍሰቱን በእጅጉ በማሳደግ ለከተማዋ ኢኮኖሚ እጅግ አበረታች ፋይዳ እያስገኘ ይገኛል።
አዲስ አበባ የብዙ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህልና እምነት መገናኛ ናት። የከተማ ልማት ይህንን ብዝሃነት የሚያከብር፣ የተለያዩ ማኅበረሰቦችን የሚያገናኝና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጠናክር በመሆኑ፤ መዲናዋ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በጋራ የሚገናኙባቸው ደማቅ መድረክ ሆናለች።
የእነዚህ ሁሉ የልማት ጥረቶች ተጨባጭ ውጤት በዓለም አቀፍ መድረክም ታላቅ ዕውቅና እያገኘ ነው። አዲስ አበባ የዘንድሮውን የ2026 የዓለም ከተሞች ቀን “የሸንሃይ አዋርድ” (Shanghai Award) ሽልማት ማሸነፍ መቻሏ፤ በመዲናዋ የተተገበረው የሰው ተኮር ልማት እይታ፣ የአካባቢ ጥበቃ ጥረት እና የነዋሪዎች የኑሮ ጥራት መሻሻል ምን ያህል የላቀ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያረጋግጥ ትልቅ ታሪካዊ ማሳያ ነው።
ይህ ሽልማት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ይበልጥ እንዲቀጥሉ፣ አካታችነት እንዲጠናከር እና የነዋሪዎች ሁለገብ ተጠቃሚነት በዘላቂነት እንዲረጋገጥ የሚያደርግ ነው።
አዲስ አበባ የተያያዘችው ሁለገብ የልማት እንቅስቃሴ የመላው አፍሪካ መዲናነቷን ክብር በላቀ ደረጃ የሚያጸና ነው። ይህም የአፍሪካውያንን ታሪካዊ ኩራት ከማደስ ባለፈ መዲናዋ የአህጉሪቱ የእድገትና የለውጥ ተምሳሌት ሆና እንድትቀጥል አስችሏታል።
ይህ ፈጠራ የታከለበትና አካታች የልማት ጉዞ መዲናዋ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነትና የከበረ የዲፕሎማቲክ ማዕከልነት ድርሻ በጽኑ መሠረት ላይ የጣለ ነው።