ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ስኬቶች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርዓያ የሚሆኑ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2019(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ስኬቶች እና የምትከተላቸው አቅጣጫዎች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርዓያ የሚሆኑ ናቸው ሲሉ በኢትዮጵያ የዴንማርክ ኤምባሲ የኢነርጂ ዘርፍ አማካሪ ቶማስ ፍሉሪን ሶረንሰን ገለጹ።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ ኤምባሲ አማካሪ ቶማስ ፍሉሪን ሶረንሰን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት የምትከተለው አቅጣጫ ትክክለኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በኃይል ልማት የምትወስዳቸው ውሳኔዎች ለሌሎች ሀገራት ማበረታቻ እንደሚሆኑ ገልፀው፣ በዘርፉ ያለው ዕድገት ለአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚሆን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ምርት ጥሩ እድገት እያሳየች መሆኑን ጠቁመው፤ በዘርፉ የተያዙት እቅዶችና የልማት አቅጣጫዎች ጠንካራ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች የረጅም ጊዜ ጠንካራ ትብብር እንዳላትም ገልጸዋል።

ትብብሩ የተቋማዊ አቅም ግንባታን፣ በተመሳሳይ ዘርፍ በሚሠሩ ተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥንና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም የሁለቱ ሀገራት ትብብር ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዴንማርክ በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች የኢትዮጵያ ጠንካራ አጋር መሆኗን አስረድተዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ትብብር የግሉን ዘርፍ በማካተት የበለጠ ሊጠናከር እንደሚችልና ይህም ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ጥቅም እንደሚያስገኝ አመልክተዋል።

ዴንማርክ ኢትዮጵያ በኃይል ልማት ላይ ለምታከናውናቸው ተግባራት ድጋፏን እንደምታጠናከር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም