በክልሉ ከ43 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመስኖ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከ43 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመስኖ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ባህር ዳር ፤ ጥቅምት 23/2019(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ከ43 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 129 የሚሆኑ የነባርና አዳዲስ መስኖ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ።
የመስኖ ልማቱ የገጸና ከርሰ ምድር ውሃን በአግባቡ በመጠቀም በመኸር ወቅት ከሚገኘው ሰብል ተጨማሪ ምርት ለማግኘት አስችሏል።
በዚህም ስንዴን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችን፣ አትክልትና መሰል አዝርዕትን በብዛት በማምረት በምግብ እህል አቅርቦት ራስን ለመቻል በሚያስችል አግባብ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የመስኖ ድሬይኔጅ ግንባታና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ጌትነት አያሌው ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በመስኖ ልማት ለኢንዱስትሪዎች ግብዓትም ሆነ ለገበያ የሚሆን ምርት እየተመረተ ነው።
ባለፉት ዓመታት ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን በማስፋፋት በተሠራ ሥራም አርሶ አደሩ በተደራጀ አግባብ ወደ ልማቱ እንዲገባ መደረጉን ገልጸዋል።
ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠልም በዚህ በጀት ዓመት 129 የሚደርሱ ነባርና አዳዲስ የመስኖ ተቋማትን ግንባታ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት በማጠናቀቅ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል።
የመስኖ ተቋማቱ 21 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው ሲሆን፣ ከ43 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የልማቱ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ከእነዚህ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት መካከልም 65 የሚሆኑትን በዚህ ዓመት አጠናቆ ወደ ልማት ለማስገባት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል።
ለመስኖ ተቋማቱ ግንባታ 5 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው፣ ማኅበረሰቡም ወሰን በማስከበር፣ በጉልበቱ፣ የግንባታ ቁሳቁስ በማቅረብና በገንዘቡ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘመናዊ መስኖ ተቋማት ግንባታ ክልሉን በዘላቂነት ከዝናብ ጥገኝነት ከማላቀቅ ባለፈ፣ በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ለማሳካት በሚያስችል አግባብ በመንግሥት በኩል በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ባለፈው ዓመት 51 የመስኖ ተቋማትን በመገንባት ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘመናዊ መስኖ ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።
በክልሉ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የመልማት አቅም እንዳለ አንስተው፣ ይህንኑ ወደ ልማት ለማስገባትም የዲዛይንና የጥናት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል።