በክልሉ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወሰዱ እርምጃዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-አቶ ሃይሉ አዱኛ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወሰዱ እርምጃዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-አቶ ሃይሉ አዱኛ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 23/2019(ኢዜአ)፦የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ ገለጹ።
አቶ ሃይሉ በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን፣በሽርካ ወረዳ፣በብርቦ ጮሌ ቀበሌ የተፈጸመውን የጽምዶ ቡድን ጥቃት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የተጎዳውን ማኅበረሰብ መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡ ያስመዘገባቸውን ድሎች በመጠበቅና በአንድነት ወደ ፊት መራመድ እንዳለበት ገልፀው፣ጥቃቱን የፈፀሙ እነዚህ ኃይሎች አዲስ የተጀመረውን የልማትና የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ በሽብር ተግባር በመሰማራት ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ብለዋል።
በ2019 ዓ.ም.ጥቅምት 14 ቀን በሽርካ ወረዳ፣ በብርቦ ጮሌ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት የንጹሐን ዜጎች ሕይወት መጥፋቱ፣የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት መቃጠሉ፣እንዲሁም ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤቶቻቸውና ከንብረቶቻቸው መፈናቀላቸው ተገልጿል።
ጥቃቱን ተከትሎ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተካሄዱ የጸጥታ ሥራዎች 73 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ መሆናቸውን፣ እንዲሁም እነዚህ ኃይሎች እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው የነበሩ ስድስት ቀበሌዎች ጸጥታቸው መረጋገጡን ገልጸዋል።
መንግሥት በአንድ በኩል የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እርምጃ እየወሰደ፣ በሌላ በኩል ከመኖሪያ ቤቶቻቸውና ከንብረቶቻቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ፣የምግብና የሕክምና ድጋፍ እያቀረበ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ተፈናቃይ ዜጎችን ወደ መኖሪያ ቤቶቻቸውና ንብረቶቻቸው ለመመለስ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መግለጫው ያመለክታል።