ባሮ - የጋምቤላ የውበት አክሊል! - ኢዜአ አማርኛ
ባሮ - የጋምቤላ የውበት አክሊል!
ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 23/2019 (ኢዜአ)፦ባሮ - የጋምቤላ የውበት አክሊል!
በሙሉጌታ ዳምጤ (ኢዜአ-ጋምቤላ)
ከኢትዮጵያ ከፍታማ ቦታዎች በመነሳት የጋምቤላ ከተማን መሀል ለመሀል አቆራርጦ ወደ ደቡብ ሱዳን በመሻገር የሶባት ወንዝ ተብሎ ከነጭ ዓባይ ጋር በመቀላቀል የመጨረሻ መዳረሻውን ሜድትራኒያን ያደርጋል።
የባሮ ወንዝ የጋምቤላ ክልል ወሰን አካባቢ ሲደርስ ገባ እና ብርብራ በሚል የሚጠሩ ወንዞችን ጨምሮ ጉዞውን ወደ ሩቅ መዳረሻው ያደርጋል። የባሮ ወንዝ የብርብር እና የገባ ወንዞች ሲቀላቀሉት የውሃው ቀለም ቀላ ስለሚል ወንዞቹ የሚገናኙበት ቦታ "ባሮ ቀላ" የሚል ስያሜ አግኝቷል፤ ሀገር አቋራጩ የባሮ ወንዝ 306 ኪሎ ሜትር (190 ማይል) ርዝመት ይጓዛል።
የጋምቤላ ክልልን የተፈጥሮ ውበት ከሰው ሕይወት፣ ከኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ከባህላዊ እሴቶች ጋር አስተሳስረው ከሚያቆዩ ታላላቅ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል የባሮ ወንዝ አንዱ ነው።
ከነ ግርማ ሞገሱ የጋምቤላ ከተማን አቆራርጦ ሲያልፍ ለከተማዋ ድምቀት ነው ማለት ይቻላል። ባሮ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛው ወንዝ ነው። የተፈጥሮ ውበት፣ የኢኮኖሚ አቅምና የሕዝብ ኑሮ ተሳስረው የሚታዩበት ታላቅ የሀገር ሃብትም እንደሆነ ይነገርለታል -ባሮ ወንዝ።
የባሮ ወንዝ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1907 ዓ.ም ጀምሮ ወደብና የጉምሩክ ጣቢያ ተቋቁሞለት ከጋምቤላ ከተማ ወደ ወረዳዎችና ሱዳን ጠረፍ የውሃ የትራንስፓርት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም በዘመናዊ መልኩ ባይሆንም ወንዙ ወደሚያቋርጥባቸው ወረዳዎችና ደቡብ ሱዳን ጠረፍ ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በአካባቢው ነዋሪዎች "ኦፔኞ" እየተባለ የሚጠራው ባሮ የጋምቤላ ተፈጥሯዊ መለያም፤ መድመቂያም ነው። የወንዙ ፍሰት፣ በወንዙ ዳርቻ የሚታየው አረንጓዴ ተፈጥሮና ከውኃው ጋር የተቆራኘው የነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሌላኛው ገጽታው ነው።
በሞቃታማ የአየር ጸባይ ወቅት በወንዙ ዳርቻ ያሉ እጽዋቶች ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችም ሙቀቱን ለማስታገስ ወንዙን ስለሚጠቀሙበት አለኝታና ታዛቸው ነው ማለት ይቻላል።
በባሮ ወንዝ ቁጥራቸው ከ51 እስከ 57 የሚደረሱ የዓሣ ዝርያዎች አሉ። በተለይም "ናይል ፐርች" በአካባቢው አጠራር "ጉር" የሚባለው ግዙፍ የዓሣ ዝርያ እስከ 100 ኪሎ ግራም ይመዝናል።
እንዲሁም "ታይገር" ፣ "ስታር" ፣ "ካት" እና "ቀረሶና" የተባሉና ሌሎች የዓሣ ዝርያዎች በውስጡ የሚገኙ ሲሆን የአዞ እና ሌሎች የብዝሃ ሕይወት ሀብቶችም መኖሪያ ነው።
በወንዙ ዙሪያ ያሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች እና ከውኃው ጋር የተያያዙ ሌሎች ሥራዎች ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የገቢ ምንጭ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
የባሮ አዞዎች በሥነ-ምህዳሩ ውስጥ የራሳቸው ሚና ቢኖራቸውም ለሰው ሕይወት አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለሆነም በወንዙ ዳርቻ እንቅስቃሴ ሲደረግ ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም አዞ እንዳለ በሚታወቅባቸው ስፍራዎች ወደ ውኃው አለመግባትና የአካባቢውን ባለሙያዎች መመሪያ መከተል የግድ ይላል።
የባሮ ወንዝ ለግብርና ልማት ሥራም ከፍተኛ አቅም ካላቸው የውኃ ሀብቶች መካከልም አንዱ ነው። በወንዙ ግራና ቀኝ ያለው ለም መሬት ለመስኖ ልማት እጅግ ጠቃሚ ነው። የአርሶ አደሮችን የምርት አቅም ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማጠናከርና የገቢ ምንጭን ለማስፋት እያገዘም ነው ።
የባሮ ወንዝ የልማት ዕድል ቢኖረውም ከወቅታዊ የውኃ መጠን መጨመር ጋር የተያያዙ ፈተናዎችም አሉት። በከፍተኛ የዝናብ ወቅት የወንዙ ውኃ ሞልቶ ሲፈስ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችን ከቄያቸው ያፈናቅላል።
አንዳንዴም በወንዙ ዳርቻ የለሙ ሰብሎች ላይ ጉዳት በማድረስ ምርትን በመቀነስ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል፤ ስለሆነም የጎርፍ ስጋትን ለመቀነስ በወንዙ የውኃ መጠን ላይ ክትትል በማድረግ በተጋላጭ አካባቢዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን ማጠናከር ያስፈልጋል።
እንዲሁም የወንዙን ዳርቻ እፅዋት መጠበቅና በጎርፍ ሊጎዱ በሚችሉ ቦታዎች ላይ የመሬት አጠቃቀምን በተቀናጀ አግባብ የመምራት አቅምን ማጎልበት አስፈላጊ ነው።
የባሮ ወንዝ ለቱሪዝም፣ ለወንዝ ዳርቻ መዝናኛና ለአካባቢያዊ ባህል ተኮር ጉብኝቶች የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ቀላል አይደለም። ጋምቤላን የሚጎበኙ ቱሪስቶች የአካባቢውን ተፈጥሮ፣ የወንዝ ዳርቻ ሕይወትና የጋምቤላን ባህላዊ እሴቶች በሚገባ ማወቅና መረዳት የሚችሉበት ሁኔታም ሰፊ ነው።
ወንዙ የጋምቤላን የተፈጥሮ ውበት ከማሳየት ባለፈ የኑሮ መሠረት፣ የልማት አቅም፣ የቱሪዝም መስህብና የብዝኃ ሕይወት መገኛ ሆኖም እያገለገለ ነው።
የባሮ ወንዝ የጋምቤላ የተፈጥሮ ውበት መገለጫ ነው። የሕዝቧ የኑሮ መጋመጃ እና የወደፊት የልማት ተስፋ መገለጫም በመሆኑ ይህን ሀብት በአግባቡ መጠበቅ ከራስ ባለፈ ለመጪው ትውልድ የተፈጥሮ ጸጋን እና የልማት ዕድልን ማስረከብም ይሆናል።