በአዳማ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት 17 ሺህ ሄክታር መሬት ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት 17 ሺህ ሄክታር መሬት ይለማል
አዳማ ፤ ጥቅምት 23/2019 (ኢዜአ)፦በአዳማ ከተማ አስተዳደር በምግብ ራስን ለመቻል በተያዘው አቅጣጫ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት 17 ሺህ ሄክታር መሬት የሚለማ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በምግብ ራስን ለመቻል እና የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ከጀመራቸው አገራዊ የኢኮኖሚ ጥረቶች መካከል የበጋ መስኖ ልማት ዋነኛው ነው።
በተለይም በአዋሽ ተፋሰስ እና በአካባቢው የሚገኙ በመስኖ የሚለሙ መሬቶችን አቅም በከፍተኛ ደረጃ የመጠቀም ስልት በመተግበር ላይ ይገኛል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደርና የከተማ ዙሪያ አምራችም ክላስተሮች አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ በስንዴና በሌሎች የብርዕ እና የጥራጥሬ ሰብሎች ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ውጤት ሲያስመዘግቡ ቆይተዋል።
የዘንድሮው የ17 ሺህ ሄክታር መሬት ልማት እቅድም የዚሁ አገራዊና ክልላዊ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ጥረት አካል ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለሙ ቂልጡ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ትልቅ እቅድ ተነድፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቷል።
ለዚህም ባለፈው መኸር እርሻ ለምቶ ለአጨዳ የደረሰውን ሰብል ሙሉ በሙሉ በመሰብሰብ በበጋ መስኖ በአትክልትና ስንዴ ዘር ለመሸፈን በየደረጃው እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በበጋ መስኖ ከሚለማው ውስጥ 10 ሺህ 200 ሄክታር የሚሆነው በስንዴ ምርጥ ዘር በኩታ ገጠም የሚለማ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀሪው መሬት ደግሞ የተለያዩ ገበያ ተኮር በሆኑ የአትክልት አይነቶች እንደሚሸፈን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት እቅዱን ለማሳካትና ስራውን ማሳለጥ የእርሻ ትራክተሮችን ጨምሮ በቂ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ይህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የበጋ መስኖ ልማቱ በወንጂ፣ በአዋሽ መልካሣና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ከ20 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እና ወጣቶች እንደሚሳተፉ አስረድተዋል።
በአስተዳደሩ ያለው ምቹ የተፈጥሮ ፀጋ በተለይም አዋሽ ወንዝ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም ዘመናዊና ባህላዊ መስኖ ልማቱን ለማስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን አውስተዋል።
በዚህ ረገድ አስተዳደሩ አርሶ አደሮችን በቴክኖሎጂ እና በምርት ማሳደጊያ ግብአት በቅርበት በመደገፍ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የበጋ መስኖ ልማት ተሳታፊ አርሶ አደሮችንም ቁጥር ለማሳደግ የውሃ መሳቢያ ሞተር አቅርቦት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊው አረጋግጠዋል።