ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ልማት የመቀየር ሥራ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል- ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

ሰመራ፣ ጥቅምት22/2019 (ኢዜአ):-በአፋር ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የተጀመሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አወል አርባ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በገቢ ረሱ ዞን ዱለሳ፣ በሃንሩካ እና ገለአሎ ወረዳዎች የተከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎችን ዛሬ ተመልክተዋል።

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር አወል እንደገለጹት በወረዳዎቹ እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ልማት ሥራዎች የህብረተሰብ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ናቸው።

ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የተጀመሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆናቸውን ገልጸው፣ ዛሬ በወረዳዎቹ በመስኖ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለዚህ ማሳያ ናቸው ብለዋል።


 

በወረዳዎቹ በመስኖ እየለሙ ካሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶች አርብቶ አደሩ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ አወል ገለጻ፣ በወረዳዎቹ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ተረክበው ወደሥራ የገቡ ባለሀብቶችም ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በጥጥና ሙዝ ልማት የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እያሸጋገሩ ይገኛሉ። 

ክልሉ በተለይ በመስኖ ውጤታማ ሥራ መስራት እንደሚቻል የዛሬው የመስክ ምልከታ አንድ ማሳያ ነው ያሉት አቶ አወል፣ ይህም ቀደም ሲል በልማት የነበሩ አመላካከትና ትርክቶች እየተቀየሩ መምጣታቸውን ያሳያል ብለዋል።


 

በመደመር መንግስት በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ለይቶ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የተጀመሩ ጥረቶች ውጤታማ በመሆናቸው ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም አስታውቀዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዋሽ ቤዝን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሀላፊ ኢንጂነር አደን አብዶ በበኩላቸው፣ "በገቢ ረሱ ዞን  በተከናወኑ የጎርፍ መከላከል ሥራዎች አካባቢውን ከሥጋት ነፃ እና የልማት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል" ብለዋል።

ለዚህም በዞኑ ዱለሳ፣ ሃንሩካና ገለአሎ ወረዳዎች 4 ሺህ 500 ሄክታር መሬትን ከጎርፍ አደጋ ነፃ በማድረግ ወደምርት ማስገባት መቻሉን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በወረዳዎቹ  ሙዝ፣ በቆሎ፣ ጥጥ፣ ሽንኩርትና ቲማቲም እየለማ መሆኑን ጠቁመው፣ በአካባቢው የውሃ ዕጥረት እንዳይከሰት ለአልሚዎቹ ውሃን በፍትሃዊነት የማከፋፈል ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዱለሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሊ ደስታ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ በወረዳው በ1ሺህ 28 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ጥጥ እየለማ ይገኛል።

አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በመስኖ ልማት ተሰማርቶ ውጤታማ መሆኑ ገቢውን በማሳደግ ተጠቃሚ እያደረገው መሆኑን ተናግረዋል።

በገለአሎ ወረዳ በጥጥ እና ሙዝ ልማት የተሰማሩት ሁመድ ጅብሪል በበኩላቸው በመሰኖ ልማት ሥራ ተጠቃሚ በመሆናቸው ልማቱን እያስፋፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዘንድሮው ዓመት ብቻ በ150 ሄክታር መሬት ላይ ሙዝ እንዲሁም በ600 ሄክታር መሬት ላይ ጥጥ እያለሙ መሆናቸውንና  ለ630 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም