በመዲናዋ የሚከናወኑ ልማቶች ሰው ተኮር እና የማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ናቸው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የሚከናወኑ ልማቶች ሰው ተኮር እና የማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ናቸው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2019 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ የሚከናወኑ ልማቶች ሰው ተኮር እና የነዋሪዎችን ማኅበራዊ ትስስር በማጠናከር ወደ ተሻለ የአኗኗር ዘይቤ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የተገነባውን የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ የተቀናጀ የመኖሪያ መንደር መርቀው ለተጠቃሚዎች አስተላልፈዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት አዲስ አበባን በጋራ፣ በትብብር እና በውጤታማነት እያለማን እንገኛለን ብለዋል።
ይህም አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ መድረክ እንድትሸለም እያስቻላት መሆኑን ተናግረዋል።
እውቅናው የሁሉም ትብብር ውጤት መሆኑን አንስተው፣ የልማት ተነሺዎች ለልማት ተባባሪ መሆናቸው ለዚህ ውጤታማነት አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።
አዲስ አበባን የማልማቱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ከንቲባዋ፣ ዛሬም ለልማት ለተነሱ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የሆነ የመኖሪያ ቤት ተገንብቶ መሰጠቱን ተናግረዋል።
ልማት ማለት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ የኢኮኖሚ አቅሙን ማጠናከርና የነገ ተስፋውን ማለምለም ጭምር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
መኖሪያ መንደሩ የነዋሪዎቹን ማኅበራዊ ትስስር በማጠናከር ወደ ተሻለ የአኗኗር ዘይቤ የሚያሸጋግርና ሰው ተኮር የአሠራር አቀራረብን የተከተለ ነው ብለዋል፡፡
ለአርሶ አደሮቹ የኑሮና የገቢ ምንጮቻቸውን የሚያሳድጉበትን ዕድል የሚፈጥሩ በርካታ አቅርቦቶችን ያካተተ መሆኑንም አብራርተዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አደፍርስ ኮራ በበኩላቸው፣ የተገነባው ቤት ነዋሪዎቹ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለማስቻል ታስቦ በዘመናዊ መንገድ መገንባቱን አስታውቀዋል።
የኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ የሚያስተሳስሩ ዘርፈ ብዙ መሠረተ ልማቶች የያዘ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በመኖሪያ መንደሩ የቤት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወ/ሮ ዘውድነሽ መስቀላ፣ የተሰጣቸው ቤት ከቀደመው የተሻለ፣ ዘመናዊ እና ውብ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኑሯቸውን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶች በተሟሉበት መንደር በመግባታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የቤት ተጠቃሚ አብራሳ ዱመቻ ናቸው፡፡
በዚህም ለከተማ አስተዳደሩ ምስጋና አቅርበዋል።