ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርናን በማዘመን የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሆሳዕና፤ ጥቅምት 22/2019 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርናን በማዘመን የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ስሩር ገለጹ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን የተመለከተ የመስክ ምልከታና ውይይት አካሂዷል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ግብርናን በማዘመን የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል።

በመደመር መንግሥት በግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻልና ገበያን ለማረጋጋት በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት መገኘቱንም ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥ ማህበረሰብ እየተፈጠረ መጥቷል ብለዋል።


 

ለዚህም ባለቤትነታቸው የአርሶ አደር የሆኑ 27 የወተት፣ የማር፣ የእንሰት እና ቅመማ ቅመም ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ መከናወኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በቀጣይም እነዚህን ውጤቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

በቢሮው የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማናጀር አቶ ከድር መሀመድ በበኩላቸው፣ ፕሮግራሙ የግብርና ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ዋና ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱም በክልሉ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን በግብርናው ዘርፍ በመደገፍ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ሌራ ከተማ ነዋሪ አርሶ አደር ከማል ሀሰን፣ በተያዘው በጀት ዓመት በማር ማቀነባበር ሥራ በኢንተፕራይዝ ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ በመንግሥት ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ከመደበኛ የግብርና ሥራቸው ጎን ለጎን ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ በመንግስት የተፈጠረላቸው ዕድል ነገን በተሻለ ተስፋ አሻግረው እንዲያዩ ያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በመንግሥት የገንዘብ ብድርና የመስሪያ ቦታ ተመቻችቶላቸው በንብ ማነብ ዘርፍ በማህበር ተደራጅተው ወደሥራ እንደገቡ የገለጸው ደግሞ በሌራ ከተማ የፍረኮት የንብ ማነብ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ኡስማን መለሰ ነው።

የማር ምርታቸውን በወረዳው ለሚገኝ የማር ማቀነባበሪያ ማዕከል በማቅረብ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገልጾ፣ የመንግስት ድጋፍ ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታውና የውይይት መድረክ ላይ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች፣ አርሶ አደሮች እና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም