በክልሉ አመራሩ ከተለመደው አሰራር ወጥቶ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ አመራሩ ከተለመደው አሰራር ወጥቶ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት አለበት
ቦንጋ፤ ጥቅምት 22/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አመራሩ ከተለመደው አሰራር በመውጣት የክልሉን ጸጋዎች በተደመረ አቅም ወደ ሃብት በመቀየር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዳለበት ተገለጸ።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅንጫፍ ጽህፈት ቤት የሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ዛሬ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት አመራሩ ከተለመደው አሰራር ወጥቶ በተደመረ አቅም የክልሉን ጸጋዎች ወደ ሃብት በመቀየር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አለበት።
ለዚህም የመደመር እሳቤን በመተግበር የሕዝቡን ሕይወት በተጨባጭ የሚቀይሩ የልማት ዕቅዶችንና ኢኒሼቲቮችን በብቃት በመተግበር መምራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ሁሉም ዞኖች ህዝብን በማወያየት ለተነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ገልጸዋል።
ከህዝቡ የተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በአግባቡ በመመለስ የሚጨበጥ ውጤት ማስመዝገብ ከአመራሩ ይጠበቃል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ባለፉት ጊዜያት የአመራሩን አቅም ለመገንባት የተሰሩ ሥራዎች የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ማሳደጉን የገለጹት የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ተክሌ፣ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን በላቀ ብቃት እንዲያስቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
በጽህፈት ቤቱ የስትራቴጂክ ሥራ አመራር ዘርፍ ሀላፊ አቶ አንተነህ አየለ የዴሞክራሲ ሥርአትን ለማጠናከር ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ የመስራት ባህል ይጠናከራል ብለዋል፡፡
የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በማጎልበት ለገዥ ትርክት ግንባታ ማዋልና እርስ በርስ የመረዳዳት ባህልን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
አደረጃጀቶችን በማጠናከር የመንግስትና የፓርቲ ተግባራትን ማሳለጥ እና በየደረጃው የተነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑ የገለጹት ደግሞ የጽህፈት ቤቱ የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አጥናፉ ሀይሌ ናቸው፡፡
የጽህፈት ቤቱ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ነጋ አበራም አመራሩ በትንሽ ውጤት ከመዘናጋት ተላቆ በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
የፓርቲ የንቅናቄ አጀንዳዎችንና ተግባራትን አቀናጅቶ በመምራት የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።