በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የመኸር አዝመራ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የመኸር አዝመራ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዳማ ፣ጥቅምት 22/2019( ኢዜአ)፡- በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን በዘንድሮው የመኸር አዝመራ የሚጠበቀውን ምርት ለማሳካት የሰብል እንክብካቤና ጥበቃ ስራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን በዋናነት በስንዴ፣ በጤፍ፣ በበቆሎ፣ በገብስ እና በቦሎቄ ምርታማነቱ የሚታወቅ ነው።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ከአርሶ አደሩ ጋር ሆኖ የተቀናጀ የሰብል ጥበቃና የእንክብካቤ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ይህ እንቅስቃሴም የዞኑን የግብርና ምርታማነት ከማሳደጉም በላይ፣ የአካባቢውን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታመናል።
የደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢብራሂም ቃሶ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ለ2018/19 የምርት ዘመን ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዋና ዋና ሰብሎች ለምቷል።
በዘንድሮው የምርት ዘመን ዋና ዋና ሰብሎች በተለይ ስንዴና የቢራ ገብስ አብዛኛው በኩታ ገጠም መልማቱንም ገልጸዋል።
ለዚህም የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችና አዳዲስ የአሰራር ቴክኖሎጂዎችን በጥቅም ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአሰላና ሻሸመኔ ክላስተር ቆላማና ወይናደጋ የዞኑ አከባቢዎች የመኸር ሰብል እየደረሰ በመሆኑ አብዛኛውን በሜካናይዜሽንና በሰው ሃይል በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በአሰላ ክላስተር ደጋማ አከባቢዎች እንዲሁም በሮቤና ግንዲሪ ደጋማ አከባቢዎች ስንዴና የቢራ ገብስን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎች እየዘረዘሩ በመሆኑ ብጫ ዋግን ጨምሮ ምርትና ምርታማነትን የሚቀንሱ የስንዴ ራስ አድርቅ በሽታዎችና አረሞችን ለመከላከል በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በተለይም ፀረ ተባይና ፀረ አረም መድሃኒቶች በሰፋፊ የኩታ ገጠም የስንዴ ሰብሎች ላይ አውሮፕላኖችን ጭምር በመጠቀም የመርጨት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የቤተሰብ ጉልበት በመጠቀም የሰብል ጥበቃና እንክብካቤ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዞኑ ደጋማው አካባቢዎች ሰብሉ ምርትና ምርታማነትን በሚቀንሱ በሽታዎች እንዳይጠቃ አርሶ አደሩ በማሳው ላይ የእለት ተእለት ክትትል ማድረግ እንደሚገባውም ሃላፊው አስገንዝበዋል።
በዞኑ በዘንድሮው የምርት ዘመን በመኸር ከለማው ዋና ዋና ሰብሎች ከ96 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አቶ ኢብራሂም ጨምረው ገልጸዋል።