ቀጥታ፡

የከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ እያሻሻለ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2019(ኢዜአ)፦ የከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ እያሻሻለ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ቢሮ ገለጸ።           

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

የአዲስ አበባ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የ2018/19 ዓ.ም በጀት ዓመት የሰብል ልማት አፈጻጸምን የመስክ ጉብኝት አድርጓል።


 

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር መሐመድ ሊጋኒ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ነው።

ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ ለአካባቢ ጥበቃና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን የመትከል ሥራ እየተስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማ ደረጃ በተቋቋመው የችግኝ ብዜት ማዕከል የአቮካዶና የአፕል ችግኞችን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን የማፍላት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የከተማ ግብርና ተሳትፎን በማሳደግ ነዋሪዎች ለራሳቸው ከማምረት ባለፈ ለገበያ የሚቀርብ ምርት እንዲያመርቱ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ምርቶቹም በየወረዳው በሚዘጋጁ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች፣ በከተማ ግብርና ምርት መሸጫ ሱቆችና በተለያዩ የገበያ ማዕከላት ለተጠቃሚው እንዲደርሱ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የከተማ ግብርና በነዋሪዎች ገቢ ላይ አወንታዊ ለውጥ እንዲመጣ ከማስቻል ባለፈ የማምረት ባህል እንዲዳብር አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል።


 

በአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የዕፅዋት ሀብት ልማት ዳይሬክቶሬት የሰብል ልማት ባለሙያ ተስፋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው፤ አርሶ አደሩን በማሰልጠን የተሻለ እንዲያመርት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ይህም ማኅበረሰቡ በራሱ አቅም ምርት እንዲያመርትና በልማቱ በንቃት እንዲሳተፍ ከማድረግ ባለፈ ከሸማችነት ወደ አምራችነት የሚያሸጋግር አስተሳሰብን ለመገንባት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።


 

አርሶ አደር ከበደ መንግሥቱ በሰጡት አስተያየትም፤ የከተማ ግብርና ሕብረተሰቡ በአካባቢው የሚያገኘውን የገበያ አማራጭ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ከሌሎች አካባቢዎች ምርት ለማምጣት የሚወጣውን የትራንስፖርት ወጪና ጊዜ ለመቀነስ እንደሚያግዝም አስረድተዋል።


 

አርሶ አደር ታቡር በቀለ በበኩላቸው፣ ባገኙት ድጋፍ የማምረት አቅማቸው 20 ኩንታል ገደማ ከነበረበት ወደ 65 ኩንታል ማደጉን አመልክተዋል።

በከተማ ግብርና ሥራ በመሳተፌ ከቤተሰቤ ጋር የተሻለ ኑሮና ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም