ቀጥታ፡

በአምቦ ከተማ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር የትምህርት ጥራትንና የተማሪዎችን ተሳትፎ እያሳደገ ነው

አምቦ፣ ጥቅምት 22/2019 (ኢዜአ)፡-በአምቦ ከተማ አስተዳደር የተተገበረው የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ለትምህርት ጥራት መሻሻልና ለተማሪዎች የመማር ፍላጎት ማደግ አስተዋጽኦ ማድረጉን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጫላ መገርሳ ለኢዜአ እንደለጹት በከተማው በ2014 ዓ.ም የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና  የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።


 

ዘንድሮም መርሃ ግብሩን በማስቀጠል በ17 ቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ 13 ሺህ 970 ተማሪዎች የምገባ መርሀግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ለመርሀግብር 34 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን አቶ ጫላ ገልጸው፣ ለዚህም የከተማዋ ቡሳ ጎኖፋና ህብረተሰቡ የላቀ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁንም 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ በምገባ መርሃግብሩ እየታየ ያለውን ውጤት ለማስቀጠል  ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በበጀት ዓመቱ የተማሪዎችን ምገባ መርሀ ግብር ለማስፋፋትና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ይበልጥ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተው በተጨማሪ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና ግብዓት የሟሟላት ሥራዎችም በመከናወን ላይ ናቸው።


 

በከተማው የሰደን ሊባን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ጫላ ቀነኒ በበኩላቸው እንዳሉት በትምህርት ቤቱ 2 ሺህ 134 ተማሪዎች በምገባ  መርሀግብሩ ተጠቃሚ ሆነዋል። 

መርሀግብሩ በተለይ ወላጆቻቸው አቅም የሌላቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሳይቸገሩ በአግባቡ እንዲከታተሉና ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዘ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተማሪዎች ምገባን ተከትሎ የደጋሚ ተማሪዎች ቁጥር እየቀነሰና የማለፍ ምጣኔ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ርዕሰ መምህሩ፣ ትምህርት የሚያቋርጡ፣ የሚቀሩና የሚያረፍዱ ተማሪዎችም  ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል ብለዋል።


 

የተማሪዎች ምገባ የወላጆችን ጭንቀትና ወጪ ከመቀነስ ባለፈ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ብቻ ሙሉ ትኩረት እንዲሰጡ አግዟል ያሉት ደግሞ የተማሪ ወላጅ አቶ ስለሺ ሚልኬሳ ናቸው።

መርሀግብሩ በተለይ አቅም የሌላቸው የተማሪ ወላጆችን ችግርና ሀሳብ በማቃለል በኩል ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረጉን የገለጹት አቶ ስለሺ፣ ብዙ ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዙንም ተናግረዋል። 


 

የትምህርት ቤቱ ተማሪ ኪሴ ደበሌ በበኩሏ የምገባ መርሀግብሩ የብዙ ወላጆችን የኑሮ ጫናን ማቃለሉን ጠቅሳ፤ እሷም ያለሀሳብ በትምህርቷ ላይ አተኩራ እንድትማር ያስቻላት መሆኑን ተናግራለች፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም