ሲዳማ ቡና ከመቻል : የአምስተኛ ሳምንት ተጠባቂ ፍልሚያ - ኢዜአ አማርኛ
ሲዳማ ቡና ከመቻል : የአምስተኛ ሳምንት ተጠባቂ ፍልሚያ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2019 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከመቻል በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የወቅቱ ሻምፒዮን ሲዳማ ቡና እስከ አሁን አንድ ጨዋታ አድርጎ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃን ይዟል።
ሲዳማ ቡና ከጋሞ ጨንቻ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ሀዋሳ ከተማ ሊያደርጓቸው የነበሩ ጨዋታዎች በሲዳማ ቡና የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎው ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘማቸው የሚታወስ ነው።
ሲዳማ ቡና በመጀመሪያ ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ባደረገው ጨዋታ የ1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።
ተጋጣሚው መቻል በሊጉ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች መካከል ዘጠኝ ነጥብ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱ ክለቦች በ2018 ዓ.ም በተገናኙባቸው የሊግ ጨዋታዎች በተመሳሳይ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል።
ጨዋታው ሲዳማ ቡና በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት፣ መቻል በድል ጉዞው ለመቀጠል የሚያደርጉት ነው።
ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሰባት ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ይዟል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በሶስት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያሸነፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በድል ጉዞው ለመቀጠል ወደ ሜዳ ይገባል።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት ይፋለማል።
ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 10 ሰዓት በሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
በአራተኛ ሳምንት ሀላባ ከተማን 6 ለ 0 በመርታት የመጀመሪያ ድሉን ያሳካው ወላይታ ድቻ በአምስት ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአንድ ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ወልዋሎ ከፋሲል ከነማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ባህር ዳር ከተማ ጋር ሊያደርጋቸው የነበሩ የሊግ ጨዋታዎች በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ምክንያት መራዘማቸው አይዘነጋም።
ወላይታ ድቻ ተከታታይ ድሉን ለማግኘት ወልዋሎ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ይጫወታሉ።
ሌላኛው የዕለቱ መርሐ ግብር ሀዋሳ ከተማ እና ጋሞ ጨንቻን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ያገናኛል።
ሀዋሳ ከተማ በሁለት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። አዲስ አዳጊው ጋሞ ጨንቻ በአንድ ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ሁለቱም ክለቦች በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት ይፋለማሉ።
ቡድኖቹ በተመሳሳይ አንድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አላቸው።