የመርሲሳይዱ ሊቨርፑል እና የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ተጠባቂ ፍልሚያ! - ኢዜአ አማርኛ
የመርሲሳይዱ ሊቨርፑል እና የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ተጠባቂ ፍልሚያ!
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2019(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሊቨርፑል እና አርሰናል ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 ላይ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ይካሄዳል።
ሊቨርፑል በዘንድሮው የውድድር ዓመት ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ በአንዱ ተሸንፎ በሶስቱ አቻ ተለያይቷል።
ቀያዮቹ በጨዋታዎቹ 11 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ስምንት ግቦች ተቆጥሮባቸው በ15 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የወቅቱ ሻምፒዮን አርሰናል በሊጉ ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች በሰባቱ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል።
በጨዋታዎቹ ላይ 13 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ አምስት ጎሎችን አስተናግዷል።
አርሰናል በ21 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
አርሰናል እና ሊቨርፑል በሁሉም ውድድሮች እስከ አሁን 246 ጊዜ ተገናኝተዋል።
ሊቨርፑል 96 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ አርሰናል በበኩሉ በ83ቱ ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል። በቀሪ 67 ጨዋታዎች ተለያይተዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ 68 ጊዜ ተገናኝተው ሊቨርፑል 26 ጊዜ ሲያሸንፍ አርሰናል በ18ቱ ድል ቀንቶታል። በቀሪ 24 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ባለፉት አምስት የሊግ የእርስ በርስ ጨዋታቸው ሁለቱም በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ሲያሸንፉ በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው የውድድር ባደረጓቸው ጨዋታዎች ሊቨርፑል አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል።
አርሰናል ካሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ የሊጉን መሪነት ከማንችስተር ሲቲ ይረከባል።
ሊቨርፑል ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል የሚል ሰፊ ግምት አግኝቷል።
የ43 ዓመቱ አንዲ ማድሊ የሁለቱን ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።