ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቦሌ ክፍለ ከተማ : የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ ግብር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቦሌ ክፍለ ከተማ : የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ ግብር
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።
ቦሌ ክፍለ ከተማ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 10 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር ቦሌ ክፍለ ከተማ መቻልን 2 ለ 1 አሸንፏል።
የወቅቱ ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመክፈቻው ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡናን 2 ለ 0 ረትቷል።
ሁለቱ ክለቦች አምና ባደረጓቸው ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
ቡድኖቹ መጋቢት 1 /2018 ዓ.ም ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኙበት የ18ኛ ሳምንት የጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦሌ ክፍለ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል።
እፀገት ግርማ እና እሙሽ ዳንኤል የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ፅግነሽ አዴ ለቦሌ ክፍለ ከተማ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ይታይበታል የሚል ግምት አግኝቷል።
በሌሎች መርሐ ግብሮች ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ከቀኑ 8 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት በባህር ዳር ስታዲየም እና ድሬዳዋ ከተማ ከልደታ ክፍለ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።