ከብሔራዊ ጥቅም ማስከበር እስከ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነት፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት - ኢዜአ አማርኛ
ከብሔራዊ ጥቅም ማስከበር እስከ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነት፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት
ጅማ፤ ጥቅምት 22/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣናዊና ዓለም መድረኮች እያሳየች ያለው ንቁ ተሳትፎና ዲፕሎማሲ መጠናከር የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት እያሳደገው መምጣቱን ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ሰላም፣ ደህንነትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ዙሪያ ታሪካዊና መሪ ሚና ያላት ሀገር ስትሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት በከፍተኛ ደረጃ በማስፋት ላይ ትገኛለች።
ሀገሪቱ የብሪክስ አባል በመሆን የተቀላቀለችበት ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የዲፕሎማሲ ክብደት ያደሰና በኢኮኖሚ፣ በንግድ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ዘርፎች አዳዲስ የትብብር በሮችን የከፈተ ክስተት ሆኗል።
በተለይም ደግሞ በሞስኮ በተካሄደው 3ኛው የአፍሪካ-ሩሲያ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ያደረገችው ንቁ ተሳትፎና የጎንዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ሀገሪቱ ከታላላቅ የዓለም ሀገራት ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማጠናከሯን ያሳያል።
ይህ መድረክ ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ፣ በኃይል ልማትና በምግብ ዋስትና ዙሪያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስክብሩ ስምምነቶችን እንድታመቻች እንዲሁም በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የራሷን የፀና አቋም እንድታንጸባርቅ ትልቅ እድል ፈጥሯል።
እነዚህም ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያላት ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከቀደመው ጊዜ በላይ እንዲያንሰራራ ማድረጉን በርካታ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ምሁራን ይገልጻሉ።
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ውጭ ግንኙነት መምህሩ ኢዶሳ ደገፈ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ብሔራዊ ጥቅሟንና የጸና አቋሟን ያስጠበቀ የጋራ መፍትሔ የማፈላለግና የመደራደር አቅሟን በከፍተኛ ደረጃ እያጎለበተች ነው።
መምህር ኢዶሳ አያይዘውም፤ ኢትዮጵያ የCOP32 ዓለም አቀፍ ጉባዔ አስተናጋጅ ሆና መመረጧንና ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ትብብር ማጠናከሯን ለአብነት አንስተዋል።
በተለይም ወደ ቀይ ባሕር የሚኖራትን ተደራሽነት ለማሳካት የምታደርገውን እንቅስቃሴ ጥንቃቄ የተሞላበት በጎ አካሄድ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ደሊል አህመድ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅምና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተሳትፎ ከቀደመው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸዋል።
በተለይም የሀገሪቱን ሰላም፣ ደኅንነትና ሉዓላዊነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በመመከት ረገድ ከሚወሰዱ እርምጃዎች ባሻገር፣ ስለ ሀገሪቱ እውነተኛ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግልጽ መረጃ በማድረስ የዲፕሎማሲ ሥራዎቿን ማጠናከሯ የተሻለ አቅም እየገነባች መምጣቷን የሚያመለክት መሆኑን አብራርተዋል።
መምህሩ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ3ኛው የአፍሪካ–ሩሲያ ጉባዔ ያደረጉት የነቃ ተሳትፎ የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት እየተስፋፋ መምጣቱን ከሚያመለክቱ ክስተቶች አንዱ አድርገው ጠቅሰዋል።
እንደ መምህሩ ገለጻ፣ የጉባዔው አስፈላጊነት በአፍሪካና ሩሲያ መካከል ያለውን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በሰፊው ዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን የዲፕሎማሲ ሚና ለማሳደግ የሚያግዝ ነው።
ይህም ሀገሪቱ ከአንድ ወገን ጋር ብቻ ተወስና ሳይሆን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ለመፍጠር የምትከተለውን የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያላት ተሳትፎ፣ ከተለያዩ ሀገራት ጋር እያሳደገች የመጣችው ግንኙነትና የራሷን አቋም በዓለም አቀፍ መድረኮች የማስገንዘብ አቅሟ እየጠነከረ መምጣቱን ገልጸዋል።