ቀጥታ፡

በአዳማ ከተማ አስተዳደር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቷል

አዳማ፤ ጥቅምት 22/2019 (ኢዜአ)፦ በአዳማ ከተማ አስተዳደር መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን የከተማው የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስታወቀ።

በአዳማ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡ ባለበት ሆኖ በበይነመረብ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችለውን መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት የማስፋፋት ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ነው የከተማው የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስተባባሪ አቶ መኩሪያ ድንቁ የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት በከተማውና በሶስት ክፍለ ከተሞች በተከፈቱ ማዕከላት የመሬት፣ የሙያ ፍቃድ፣ የገቢና የባንክ አገልግሎቶችን ጨምሮ 138 አገልግሎቶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየተሰጡ እንደሚገኙ አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከንግድ ፍቃድ (E-TRADE) ብቻ 37 ሺህ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው በበይነ መረብ  ማስተናገድ መቻሉንም አንስተዋል።

አገልግሎቱን በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ ህንፃዎች እየተገነቡ መሆኑን ገልጸው፤ እስከ ሁለተኛው መንፈቅ ዓመት ድረስ ሁሉንም ዓይነት አገልግሎቶች በበይነመረብ ለማቅረብና የተንቀሳቃሽ አገልግሎትንም ለመጀመር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኢዜአ ያናገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ ማዕከሉ አገልግሎቶችን ባንድ ማዕከል በማቅረቡ እንግልትን፣ መመላለስንና ብልሹ አሰራሮችን ማስቀረቱን ገልጸዋል።

ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል አቶ ጌዲዮን ማሬ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ፍቃድ ለመጠየቅ ወደ ማእከሉ መምጣታቸውን ገልጸው፤  ካሁን በፊት የመንግሥት አገልግሎት ለማግኘት ከቢሮ ቢሮ መመላለስና ረጅም ጊዜ መቆየት የተለመደ ነበር ይላሉ።

አሁን ግን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ይህንን  የቀየረ እና  ፈጣን፣ ቀልጣፋና ያለ ምንም እንግልት አገልግሎት በመስጠቱ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ሌላኛዋ በማዕከሉ ያገኘናቸው  ተገልጋይ ወይዘሮ ተስፉ ብሩ፤ የአንድ ማእከል አገልግሎት  በጣም ፈጣንና ምንም ማጉላላት የሌለበት ሆኖ እንዳገኙት ጠቅሰዋል።

የመጡበትን የወሳኝ ኩነት ጉዳይ በደቂቃዎች ውስጥ  ጨርሰው መውጣታቸውን ገልጸው፤ በዚህም  በእውነቱ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ የአሰራር ቅልጥፍናን ለማሳደግ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲያጠናክር እንዲሁም የመልካም አስተዳደር መርሆዎችን በተቋማት ውስጥ በተግባር ለማስፈን ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ተገልጋዮቹ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም