ምልዑነት የተላበሰ ዜጋ ለመፍጠር ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ምልዑነት የተላበሰ ዜጋ ለመፍጠር ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ምልዑነት የተላበሰ ዜጋ ለመፍጠር ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በታሪክና ፖለቲካ ተመራማሪው ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) የተጻፈው ምልዑነት የተሰኘው መጽሀፍ ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ደራሲው ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ለረጅም ጊዜ ህዝብን ያገለገሉ ናቸው።
መጽሐፉም ህዝብን ሲያገለግሉ የተመለከቱትን እውነት የሚዳስስ መሆኑን ገልጸው፤ የተከፋፈለ ሀሳብን ማስወገድ፣ በጋራ መስራትና የጋራ ትርክት መገንባት እንደሚገባ ያስገነዝባል ብለዋል።
የተደመረ አቅም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ልዩነቶችን የጥንካሬ ምንጭ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የወጣቶች ፈጠራና የምሁራን ሀሳብ ምክንያታዊ ትውልድ ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ምልዑነት የተላበሰ ማህበረሰብ መገንባት የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።
መጽሐፉ የመደመር እሳቤን የሚያጎለብት ለትውልዱ ብርሀንን በማመላከት የተደመረ ሀሳብ ምሉዕ ማህበረሰብ እንደሚፈጥር ያሳያል ብለዋል።
የታሪክና ፖለቲካ ተመራማሪው ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
የመጽሀፉ ደራሲ የታሪክና ፖለቲካ ተመራማሪው ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር)፤ መጽሀፉ የተሟላ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማስተላለፍ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በርዕዮተ ዓለም ፍጭቶች ስትተራመስ መቆየቷን አስታውሰው፤ ዛሬ ላይ ሰዋዊ አካሄድን እየተከተለች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
መጽሀፉ የተሟላ ህብረተሰብ ለመፍጠር ያለመ እና የተለያዩ የመፍትሄ ሀሳቦችን የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል።
በመጽሀፉ ላይ ዳሰሳ ያቀረቡ ምሁራን መጽሀፉ ወደ ፊት መሄድን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ልማት ጥናት ኮሌጅ ዲን ዋቅጋሪ ነገሪ (ዶ/ር)፤ መጽሀፉ 21ኛው ክፍለ ዘመንን በሚመጥን መንገድ እንዴት መሄድ አለብን የሚለውን የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል።
መጽሀፉ የመደመር እሳቤን የሚያጎለብት እና ለትውልዱ ብርሀንን የሚያሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የማህበራዊ ሳይንስ እና የቢዝነስ ጉዳዮች አጥኚ ደምሴ ገረመው በበኩላቸው ፤ የተደመረ ሀሳብ ምሉዕነትን የሚያመጣ መሆኑን እና ምሉዕ ማህበረሰብ እንደሚፈጥር መጽሀፉ በጉልህ እንደሚዳስስ ገልጸዋል።
መጽሀፉ የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንደሚያመላክትም አንስተዋል።
የምሉዕነት መጽሐፍ በአራት ክፍሎችና በ16 ምዕራፎች የተዋቀረ ሲሆን፣ በ328 ገጾች ተሰንዶ ለአንባቢያን ቀርቧል።