ቀጥታ፡

የመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዘ ነው -ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

 ሰመራ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ በአፋር ክልል የመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዘ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በክልሉ ገቢ ረሱ ዞን በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ተመልክተዋል ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ የመስኖ ልማት ስራ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዘ ነው።

በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ እየተካሄደ ያለው የመስኖ ልማት ስራም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በወረዳው በ100 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ያለው ጤፍ ጥሩ ጅማሮ መሆኑን ጠቁመው በተመሳሳይ በ150 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ያለው በቆሎም በመልካም ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል። የመስኖ ልማቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አደን በልአ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በወረዳው ዘንድሮ በበጋ መስኖ 9 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎች እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

እስካሁን ባለው ሂደት 4 ሺ 500 ሄክታር መሬት መልማቱን ተናግረዋል።


 

የበጋ መስኖ ልማት አርብቶ አደሩን ከእንስሳት እርባታ በተጓዳኝ በግብርና ስራ በመሰማራት ተጠቃሚ  እያደረገው መሆኑን አመልክተዋል።

የወረዳው አርብቶ አደሮች በመስኖ በመታገዝ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እንዲሁም  ሀብሀብና ሙዝ  በሰፊው በማምረት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አስታውቀዋል።

በመስክ ምልከታው የክልሉ፣ የዞንና የወረዳ የስራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም