የአዲስ አበባ ከተማ አስደናቂ ክትመትና የመሰረተ ልማት ዕድገት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም አርዓያ ይሆናል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ አስደናቂ ክትመትና የመሰረተ ልማት ዕድገት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም አርዓያ ይሆናል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦የአዲስ አበባ ከተማ አስደናቂ ክትመትና የመሰረተ ልማት ዕድገት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርዓያ ይሆናል ሲሉ የታንዛኒያ የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት ልዑካን ቡድን አባላት ገለጹ።
ከጥቅምት 18 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤቶች የልምድ ልውውጥ መድረክ ተጠናቋል።
የታንዛኒያ የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት ልዑካን ቡድን አባላት ከልምድ ልውውጡ ባሻገር በአዲስ አበባ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም በመዲናዋ ባለው ፈጣን የመሰረተ ልማትና የከተሜነት ዕድገት እንዲሁም በሳቢነቷ ተደንቀዋል።
የልዑካን ቡድኑ አባል ዶርካስ ዳዊዶ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለጎብኝዎች ደግሞ አስደማሚ ነው።
በሁሉን አቀፍ መሰረተ ልማትና በአረንጓዴ ሥፍራዎች ያጌጠች መሆኗን ገልጸው፤ ታንዛኒያ የኢትዮጵያ የልማት ተሞክሮ እንድትወስድ የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል።
የታንዛኒያ የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት የሕግ ባለሙያ ኤልያድ ኢ-መንደም፤ የከተማዋን ፈጣን ዕድገትና የኢትዮጵያውያንን ታሪካዊ አርበኝነት የሚያስደንቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በእግር ጉዞ የተለያዩ አካባቢዎችን መጎብኘታቸውን ገልጸው፤ የመዲናዋ መሠረተ ልማት፣ የመንገዶችና የሕንፃዎች ግንባታ በማራኪ ሁኔታ ተለውጧል ብለዋል።
አንድነት ፓርክንና የዓድዋ ድል መታሰቢያን በጎበኙበት ወቅት ያዩት የኢትዮጵያውያን ጽናት እና ቁርጠኝነት ለአፍሪካውያን ትልቅ ትምህርት እንደሚሰጥ አንስተዋል።
የታንዛኒያ ፋይናንስ ሚኒስቴር የዕቅድ መምሪያ ኃላፊ ኤልያስ ሬይመንድ ማፑንዳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በከተማ ዕቅድና በልማት ዘርፍ ያሳየችው ስኬት ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት ይሆናል ብለዋል።
የታንዛኒያ መንግሥት ከኢትዮጵያ የልማትና የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች በርካታ ልምዶች መቅሰም እንደሚችል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ያሳዩትና አሁንም የሚያንፀባርቁት አንድነት ለሀገር ዕድገትና ልማት መሰረት መሆኑን ገልጸው፤ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ ፤ታላቅ ርዕይ