ቀጥታ፡

አዲስ አበባ የ2026 የከተሞች ዘላቂ ልማት ዓለም አቀፍ ሽልማት ማግኘቷ ለኢትዮጵያ ታላቅ ኩራት ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦አዲስ አበባ የ2026 የከተሞች ዘላቂ ልማት ዓለም አቀፍ ሽልማትን (2026 Global Award for Sustainable Development in Cities) ማግኘቷ፣ በከተማዋ የታየውን እድገት፣ ዘላቂ ልማትና ቀጣይነት ያለው ለውጥ የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ታላቅ ኩራት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ይህ ደግሞ ወደፊት ለመመልከት መልካም አጋጣሚ ነው ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

የእያንዳንዱን ከተማ ልዩ ታሪክ፣ ቅርስና ማንነትን እየጠበቅን ዘመናዊ፣ አካታችና ዘላቂ ከተሞችን መገንባታችንን መቀጠል ይኖርብናል ያለው ጽህፈት ቤቱ የከተማ ልማት ከመሠረተ ልማት በላይ መሆኑንም አመልክቷል።

የከተሜነት ባህልን ማሳደግ፣ ጥራት ያላቸው የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችን መፍጠር እና ከተሞቻችንን ለመኖርና ለመሥራት የተሻሉ ቦታዎች ማድረግ ማለት ነውም ብሏል።

ራዕያችን ከአዲስ አበባ ባሻገር ሊሰፋ ይገባል፤ ከሐረር እስከ ባሕር ዳር፣ ከሐዋሳ እስከ ጅማ፣ ከአርባ ምንጭ እስከ ድሬዳዋ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ከተማ የዘላቂ ከተማ ልማት ማሳያ የመሆን አቅም አለው ሲልም ገልጿል።

ዛሬ አዲስ አበባ፤ ነገ ደግሞ ለእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ከተማ አዲስ ምዕራፍ። ከታሪካቸው ሳይነጠሉ የወደፊቱን ጊዜ የሚመጥኑ ከተሞችን እንገንባ ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መልዕክት አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም