በኢትዮጵያና ጅቡቲ ኮሪደር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ኔትወርክ ለመዘርጋት የጋራ ኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና ጅቡቲ ኮሪደር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ኔትወርክ ለመዘርጋት የጋራ ኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈጸመ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያና በጅቡቲ ኮሪደር ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ኔትወርክ ለመዘርጋት ከሶስት የውጭ ኩባንያዎች ጋር የጋራ ኢንቨስትመንት ስምምነት መፈጸሙን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ-ጅቡቲ የትራንስፖርት መስመር ላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች ቻርጅ መሙያ አውታር ለመዘርጋት ከቻይና ሮድ ኤንድ ብሪጅ ኮርፖሬሽን፣ ከቤጂንግ ፎርኤቨር ቴክኖሎጂ ሊሚትድ እና ከሁዋዌ ቴክኖሎጂስ ጋር ስምምነት ተደረጓል።
ይህ የትብብር ስምምነት ቀደም ሲል የኃይል ፍላጎትን በማጥናት፣ ጣቢያዎቹ የሚገነቡባቸውን አካባቢዎች በመለየት እንዲሁም የቴክኒክ ሞዴሎችን እና የጊዜ ሰሌዳዎችን በማውጣት ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል።
ስምምነቱ በኮሪደሩ ላይ የተሽከርካሪ መሙያ ጣቢያዎችን በማቀናጀት ተደራሽነታቸውን ለማስፋት ያለመ እንደሆነም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር፣ የባለሙያዎች አቅም እንዲያድግ እና የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በዚህም አረንጓዴ የትራንስፖርት ሥርዓትን በማስተዋወቅ የነዳጅ ጥገኝነትንና ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ፣ የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል እና የታዳሽ ኃይል አጠቃቀምን ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።