በክልሉ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ በሲዳማ ክልል በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራርና ድጋፍ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።
"አይበገሬነት ከቤት ይጀምራል" በሚል መሪ ሐሳብ የአደጋ ስጋት ቀን በሀዋሳ ተከብሯል።
በወቅቱም የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራርና ድጋፍ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ኃይሉ ሐሰና እንዳሉት፣ በክልሉ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል።
በክልሉ የመጠባበቂያ እህል ክምችትን ለማሳደግ የወል መሬትን በማረስ እህል የማምረት ተግባሩ በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አክለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በካላሞ ኢንሼቲቭ መላውን የክልሉን ነዋሪ በማሳተፍ በፎጮ ባህላዊ ሥርዓት ሕብረተሰቡ በእህል፣ በቁሳቁስና በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የመጠባበቂያ ክምችቱን የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በዚህም ለአንድ ጊዜ 320 ሺህ ሰዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ከ8 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰው፣ ሕብረተሰቡም በፎጮ ባህላዊ ሥርዓት ከ11 ሺህ ኩንታል በላይ እህል ለመጠባበቂያ ክምችቱ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል የመንግሥት ረዳት ተጠሪ አቶ በላይነህ በየነ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልል ደረጃ ማንኛውም አደጋ ቢያጋጥም በራስ አቅም መሸፈን የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ የተጀመረውን በምግብ እህል ራስን በመቻል ከተረጂነት ለመላቀቅ የተያዘውን ግብ ስኬታማ ለማድረግ እንደ ክልል በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ የሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ረዳት የመንግሥት ተጠሪ አቶ ዱሬሳ ሌዳሞ በበኩላቸው፣ በዞን ደረጃ ከተረጂነት ለመላቀቅ በተያዘው አቅጣጫ መሠረት ለአደጋ ጊዜ የሚደርስ 63 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል በክምችት ላይ እንዳለ ገልጸዋል።
በዞኑ በመኸር የለማውን ሳይጨምር 10 ሺህ ኩንታል ምርት ለአደጋ መጠባበቂያ ክምችት መኖሩንም እንዲሁ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ እየተከበረ ባለው የአደጋ ስጋት ቀን መርሐግብር ላይ የክልሉ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።