ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የዓለም አቀፍ የተጓዦች ትስስር ቴክኖሎጂን ልትተገብር ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ወንጀለኞች ተላልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትስስር ቴክኖሎጂን ልትተገብር መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

በኢንተርፖል የለማው ይሄው ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትስስር ቴክኖሎጂ ስርዓት ሽብርተኝነትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ሰርተው የተደበቁ ወንጀለኞች ህግን ተከትሎ ለአባል ሀገራት ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረግ የሚያስችል ነው። 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በቀጣናው በገነባው ጠንካራ የወንጀል መከላከል አቅምና ከኢንተርፖል ጋር ባለው የተቀናጀ ትብብር ለአባል ሀገራት የሕግ አስከባሪዎች ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው ስልጠና በመስጠት ከሚታወቀው የኢንተርፖል ግሎባል አካዳሚ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች በቴክኖሎጂ የታገዙና ውስብስብ የሆኑበት ዘመን ተፈጥሯል። 

እነዚህን ውስብስብ ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎች ለመቆጣጠርና ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም ኢንተርፖል ድንበር ዘለል ወንጀሎችን መከላከልና ወንጀል ሰርተው የተደበቁ አካላት ተላልፈው የሚሰጡበት ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትስስር ቴክኖሎጂ ስርዓት ማልማቱን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው በሽብርተኝነት ወይም በሌላ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል የሚፈለጉ አካላትን በየትኛውም ሀገር ላይ በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀለኞችን ባሉበት ቦታ ለመያዝ ከኢሚግሬሽንና አየር መንገድ ጋር በሚኖረው ቅንጅት ላይ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው ወንጀለኛ የትም ቦታ መደበቅ እንዳይችል የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ ገቢራዊ ለማድረግ በሂደት ላይ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እንዲጠናከር በማድረጋቸው ከኢንተርፖል ጋር ጥብቅ ትብብር መፍጠር ማስቻሉን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በሰራው የተቀናጀ ዘመቻ አንድ ወንጀለኛ ተይዞ ለኢትዮጵያ ተላልፎ እንዲሰጥና ለህግ እንዲቀርብ ተደርጓል ብለዋል።

ኢትዮጵያም በተለያዩ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የሚፈለጉ አካላትን ህግና ስርዓት በመከተል ለሀገራት ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረጓን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው በቀን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመከታተል ወንጀለኞችን በቀላሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በደረቅ ወደብና በሌሎች የትራንስፖርት ዘርፎች የሚስተዋሉ የሽብር እንቅስቃሴዎችና ወንጀሎችን ተከታትሎ መያዝ ያስችላል፤ በቅርቡም ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም