የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎች መስፋፋት የቢሾፍቱን የቱሪዝምና አረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎች መስፋፋት የቢሾፍቱን የቱሪዝምና አረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ ያግዛል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦በቢሾፍቱ ከተማ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎች መስፋፋት የቱሪዝምና አረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ እንዲያድግ ያግዛል ሲሉ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ አዳማ፣ ባቱ እና ሀዋሳ እንዲሁም አዲስ አበባ አምስት ቦታዎች ያስገነባቸውን የኤሌክትሪክ ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎች እያስመረቀ ይገኛል።
የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ፤ በቢሾፍቱ ከተማ የተገነቡ የኤሌክትሪክ ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎች ምረቃ ወቅት ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ቢሾፍቱ ከአዲስ አበባ 47 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ፣ በተፈጥሮ ሀብቶቿና በሐይቆቿ የታወቀች የቱሪዝምና የኢኮኖሚ ማዕከል ናት።
በከተማዋ የተቋቋሙት ጣቢያዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በቀላሉ ቻርጅ ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውን አውስተው፤ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ቢሾፍቱ የሚመጡ ተጓዦች በከተማዋ በምቾት ቆይታቸውን እንዲያደርጉ እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም የነዳጅ ፍላጎትን ለማቃለል፣ የአየር ብክለትን ለመቀነስና አረንጓዴ ልማትን ለማጠናከር አስፈላጊ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ በቢሾፍቱና በአካባቢው ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎች ሲገነቡ ለፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልጉ ቦታዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ እስከ ሥራ ማስጀመር ድረስ የከተማ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው በበኩላቸው፤ በስድስት ዋና ዋና ከተሞች የተገነቡ 11 ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ፈጣን ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎች በአንድ ጊዜ 96 ተሽከርካሪዎችን የመሙላት አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል።
ተቋሙ በአንድ ጊዜ እስከ 150 ተሽከርካሪዎችን የኤሌክትሪክ ቻርጅ ለማድረግ የሚስችል አቅም መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎች መስፋፋት የንጹህ ኢነርጂ አጠቃቀምን ከማበረታታት ባለፈ የአየር ብክለትንና በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በቀጣይም በመቀሌ፣ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በጅግጅጋ፣ በድሬዳዋ፣ በጅማ፣ በአርባ ምንጭና በሌሎች ከተሞች ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን ለማስፋፋት ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።