ቀጥታ፡

በመደመር መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ተወዳዳሪ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው- ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን

ቦንጋ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ በመደመር መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ተወዳዳሪ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን ገለጹ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ አዋጅ የማስተዋወቂያ መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን እንዳሉት፣ የመደመር መንግሥት ግብርናውን ከልማዳዊና ከእጅ ወደ አፍ አሠራር በማላቀቅ ዘመናዊና ተወዳዳሪ ለማድረግ የዘረጋቸው አሠራሮች ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጡ ነው።

በዚህም ረገድ የግብርናው ዘርፍ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርምን በመከተል፣ የዘርፉን ዕድገት እውን ለማድረግ አስቻይ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችን እንዲሁም የልማት ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ይህም የመልማት ጸጋን በአግባቡ በመጠቀም የግብርናና የገጠር ትራንስፎርሜሽን ብሎም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፣ የዘርፉን ተዋንያን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን አመልክተዋል።

የግብርና ቢዝነስ ኩባንያዎች መስፋፋት የገጠር ኢኮኖሚን በማነቃቃት የሥራ ዕድሎችን የሚያሰፋ፣ የኢንዱስትሪና የግብርና ትስስርን በዘላቂነት የሚያጠናክርና የገጠር ትራንስፎርሜሽን እውን እንዲሆን የሚያስችል ነውም ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) በበኩላቸው፡ አዋጁ ለአርሶና አርብቶ አደሩ በቂ ድጋፍ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን በዘላቂነት ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት አርሶ አደሩ ቀደም ሲል ከነበረው የተበታተነ አሠራር ተላቅቆ በክላስተር ማምረት በመቻሉ ምርታማነቱ እየጨመረ ቢመጣም፣ ተጠቃሚነቱን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሕጋዊ ሰውነት ማግኘት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ይህን መነሻ በማድረግ አዋጁ መዘጋጀቱን አንስተው አዋጁ የአነስተኛ ይዞታ አምራቾችን ማደራጀት ወደ መካከለኛ አልሚነት በማሻገር እንዲሁም የግብዓትና ቴክኖሎጂ አቅርቦትን በማሳለጥ ገቢን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣ አርሶ አደሩ ከተለመደው አመራረት ተላቅቆ በክላስተር በማልማት አምርቶ ከመብላትና ከመሸጥ ባለፈ ወደ ኩባንያ ደረጃ እንዲሸጋገር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በክልሉ ከ3 ሺህ 400 በላይ አርሶ አደሮችን በሁለት ኩባንያዎች በማደራጀት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

በመድረኩም የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ተክሌ በዛብህን ጨምሮ የክልልና የኢንስቲትዩቱ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም