ቀጥታ፡

በተዘዋዋሪ ችሎትና በአማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት እያገኘን ነው- የጋሞ ዞን ነዋሪዎች

አርባ ምንጭ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ በተዘዋዋሪ ችሎትና በአማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋሞ ዞን ተገልጋዮች ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋሞ ዞን ተገልጋዮች፤ በተዘዋዋሪ ችሎትና በአማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከተገልጋዮች መካከል የካምባ ወረዳ ነዋሪ አቶ ገላዬ ጋምአ፤ በየአካባቢው የተመሠረቱት ተዘዋዋሪ ችሎቶች ከልማት ሥራችን ሳንለይ ፍትህ በቅርበትና በፍጥነት እንድናገኝ አስችለውናል ብለዋል።

ይህም ከዞን ማዕከል ፍትህ ለማግኘት ስንሄድ ሲያጋጥመን ከነበረው የጊዜ ብክነትና እንግልት ታድጎናል ነው ያሉት፡፡


 

በየቀበሌው የተደራጀ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት መኖሩ ቀልጣፋ ፍትህ እንድናገኝ እያስቻለን ነው ያሉት ደግሞ የቁጫ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አስናቀች ይስሃቅ ናቸው።

ይህ ሥርዓት ሁለቱንም ወገኖች አሸናፊ በማድረግ ቂምና ቁርሾን በማስወገድ ዘላቂ ሰላምና ወዳጅነት እንዲኖር በማድረግ የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ግንሶ ግዛው፤ በተዘዋዋሪ ችሎት፣ በአማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎችና የማስቻያ ስፍራዎችን ምቹና ሳቢ በማድረግ የሕዝቡን እርካታ ለማረጋገጥ በተከናወነው ተግባር ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል።

በዞኑ በሰባት ማዕከላት ተዘዋዋሪ ችሎቶች እየተሰጡ መሆኑን አንስተው፣ ተገልጋዩ ሕብረተሰብ ፍትህ በቅርበት ከማግኘት ባለፈ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተጠቃሚ እየሆነ ነው ብለዋል።

በክልሉ አዋጅ ቁጥር 63/2017 መሠረት በዞኑ ካሉ 335 ቀበሌዎች በ182 ቀበሌዎች በአማራጭ ሙግት መፍቻ ዘዴ ባህላዊ ዳኞች የተደራጀ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

በተለይ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴው ሁሉንም ዓይነት የፍትሐ ብሔርና ቀለል ያሉ የወንጀል ጉዳዮችን የማስቻል ዕድል ያለው በመሆኑ ተገልጋይ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ከማድረግ ባለፈ የፍርድ ቤቶችን የሥራ ጫና ይቀንሳል ብለዋል።

በአንደኛው ሩብ ዓመት ፍርድ ቤቶች ዝግ ቢሆኑም ከቀረቡ 5 ሺህ 925 መዝገቦች መካከል 1 ሺህ 477ቱ ውሳኔ ያገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም 530 መዝገቦች በአማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴ በእርቅ እንዲያልቁ መደረጉንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም