ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ ከሁዋዌ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤሪክ ዩዋን ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ ከሁዋዌ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤሪክ ዩዋን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ የሁዋዌ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን በቅርቡ ሥራ ከጀመሩት ኤሪክ ዩዋን ጋር ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በውይይታችን ወቅት መንግሥት የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ ለማስቀጠልና ለማፋጠን እየሠራቸው ያሉ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች እጅግ አበረታች መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸውልኛል ብለዋል።
ሁዋዌ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይና ብሔራዊ የልማት ግቦቻችንን ለማሳካት በምናደርገው ጥረት ውስጥ፣ በተለይም በአይሲቲ መሠረተ ልማትና በግንኙነት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ጉዞም ከሁዋዌ ጋር በትብብር፣ በብሔራዊ ባለቤትነት፣ በዘላቂነት፣ በደኅንነትና በአካባቢያዊ እሴት ፈጠራ መርሆዎች ላይ ተመሥርተን በምንሠራባቸው የትብብር መስኮች ዙሪያ መክረናልም ብለዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታችን በእመርታ እየተጓዘ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ሁዋዌም ለዚህ ዕድገት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ እና ያለንን የሥራ ግንኙነት አጠናክረን ለመቀጠል ተስማምተናል ሲሉም ገልጸዋል።