በክልሉ በግብርናው መስክ ያሉ እድሎችን በመለየት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በግብርናው መስክ ያሉ እድሎችን በመለየት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ
ዱራሜ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግብርናው መስክ ያሉ እድሎችን በመለየት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ የ2019 በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ንቅናቄ መድረክ በዱራሜ ከተማ አካሂዷል።
በወቅቱም የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር እንደገለፁት፣ ክልሉ በግብርናው መስክ ያሉትን ዕድሎች በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል በትጋት እየሰራ ነው።
በዚህም ከድህነት የተላቀቀ፣ የምግብ ሉዓላዊነቱን ያረጋገጠና በኢኮኖሚ ራሱን የቻለ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚያስችለውን የመደመር መንግሥት እሳቤ እየተገበረ ይገኛል ብለዋል።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀና በውሃ አማራጮች ላይ የተመሠረተ የግብርና አሠራርን ተግባራዊ በማድረግ ትርፍ አምርቶ ለገበያ በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት ረገድ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አመራሩ በግብርናው መስክ እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የመስኖ ተቋማትን በማጠናከር የግብርና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግና ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲውሉ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ የገለጹት ደግሞ የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ናቸው።
የንቅናቄ መድረኩ በክልሉ የሚገኙ የመስኖ መሠረተ ልማት አውታሮች ያሉባቸውን ማነቆዎች በመፍታት በሙሉ አቅማቸው እንዲያለሙ በማድረግ በዘርፉ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የጋራ ተግባቦት መፍጠርን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ 12 የመስኖ ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅማቸው፣ 88ቱ ደግሞ በከፊል እያለሙ እንደሚገኙ፣ እንዲሁም ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ያልጀመሩ 11 የመስኖ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የመስኖ ፕሮጀክቶቹን ከደለል የመታደግ፣ የመጥረግና የውሃ አጠቃቀም ሂደቱን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ በማድረግ በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የምሥራቅ ጉራጌ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ መሐመድ አማን እንደገለጹት፣ በዞኑ ከ1 ሺህ 300 ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች በመስኖ ይለማል።
የመስኖ ልማቱ አርሶ አደሩ በወቅት ሳይገደብ አልምቶ እንዲጠቀም ከማስቻሉም በተጨማሪ ገበያን በማረጋጋት ረገድ ዋነኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በክልሉ በ2019 የበጋ መስኖ ልማት ሥራ 149 ሺህ ሄክታር ማሳን በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከ38 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ግብ ተጥሎ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መገባቱን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።