ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚረዱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው 

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦በጋምቤላ ክልል የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚረዱ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ። 

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡቦንግ ኡጉታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የትምህርት ግብዓቶችን የማሟላትና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ ነው።


 

በትምህርት ዘመኑ በ6ኛና በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናዎች ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተናም ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

የቢሮ ሀላፊው አክለውም በትምህርት ዘመኑ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች የተማሪ መጽሀፍ ጥምርታን አንድ ለአንድ ለማዳረስ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።


 

የጋምቤላ ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ኚቡል ጊቤ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት  ከወዲሁ ሙሉ ጊዜዋንና ትኩረቷን ለትምህርት ዝግጅትና ጥናት መስጠትዋን ተናግራለች።

ዘንድሮ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀም እያጠናች መሆኗን የገለጸችው ደግሞ የጋምቤላ ከተማ ኢሊይ 2ኛ ደረጃ  ትምህርት ቤት ተማሪ ፈትያ ጃሃልድ ናት።


 

የጋምቤላ ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ዋሲሁን ደጀኔ እና የጋምቤላ ከተማ ኢሊይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አብራሃም ኡቶይ በበኩላቸው፤  በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተማሪዎችን ውጤት ከፍ ለማድረግ በመደበኛና በተጨማሪ ክፍለ ጊዜ ተማሪዎቻቸውን  የማብቃት ስራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም