ቀጥታ፡

የተፈጥሮ ገጸ በረከት የሞላበት አስደናቂ ምድር

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ የተፈጥሮ ገጸ በረከት የሞላበት አስደናቂ ምድር

በሙሉጌታ ዳምጤ

ከአዲስ አበባ በ700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በተፈጥሮ ሃብት የታደለ፣ መልማት የሚችል ሰፊ ምድር ያለው፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ፣ ለዓሳ ሀብት ልማት ብሎም ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ አካባቢ ነው። እዚህ ክልል መጥቶ ምን ጠፍቶ! ከባሮ ወንዝ ዓሳ አጥምዶ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ጥጥ፣ ሰሊጥ እና ማሾ አምርቶ በአረንጓዴው ስፍራ ተዝናንቶ የሚኖርበት ነው።

በባሮ ወንዝ ፍሰት፣ በደኖች የነፋስ ሽውታና ውበት፣ በዱር እንስሳት፣ የሕዝቡ ባህላዊ እሴት የክልሉ የብዝሃነት ምልክቶች ናቸው። የወንዞች በረከት፣ የደኖች ጥላና የሕዝቦች አንድነት የተዋሃዱበት ጋምቤላ ክልል የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ውበትና የልማት ተስፋ ማሳያ መሆኑን መናገር ይቻላል።

የጋምቤላ ልዩ የተፈጥሮ ሃብት፣ የእድገትና የማንሰራራት መሰረት የሚሆን የሀገር ሃብት የሚገኝበት መሆኑም ይታወቃል። በመሆኑም የክልሉ የብዝሃ ህይወት ሃብት በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት /ዩኒስኮ/ በባዮስፌር ሪዘርቭነት የተመዘገቡ የተፈጥሮ ደን ሃብት ባለቤት እንዲሆን አስችሎታል።


 

የተፈጥሮ ገጸ በረከት የሞላበት አስደናቂው ምድር ጋምቤላ፤ በማጃንግና አኙዋሃ ዞኖች የሚገኙ ጥብቅ የተፈጥሮ የደን ሃብቶቹ  በ’’ዩኒስኮ በባዮስፌር ሪዘርቭነት’’ የተመዘገቡ ናቸው። እነዚሁ በባዮስፌር ሪዘርቭነት የተመዘገቡት የተፈጥሮ ጥብቅ ደኖች በውስጣቸው በርካታ የዕፅዋት፣ የእንስሳት፣ የውሃና ሌሎች የብዝሃ ህይወት ሀብቶችን አቅፈው ይዘዋል።

ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖቹ የአካባቢውን ስነ-ምህዳርና የአየር ንብርት ለውጥ ከመጠበቅ ባለፈ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ትልቅ አቅም ናቸው። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2017 በዩኒስኮ በባዮስፌር ሪዘርቭ የተመዘገበው የማጃንግ ጥብቅ የተፈጥሮ የደን ሃብት በቡሬ ሐይቅ፣ በጀይና በዋኪ ፏፏቴዎች፣ በጊሎ ወንዝና በሌሎችም የብዝሃ ህይወት ሃብቶች ያጌጠ ነው።

ከክልሉና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት መልካ ኢትዮጵያ የተሰኘ ግብር ሰናይ ድርጀት ባካሄደው ጥናት መሰረት በጥብቅ ደኑ ውስጥ ከ550 በላይ የዕፅዋት፣ 33 የአጥቢ እንስሳት፣ 130 የአዋፋትና ሌሎችም የብዝሃ ህይወት ሃብቶች አሉት።


 

በ2025 በዩኒስኮ የተመዘገበው የአኙዋሃ ባዮስፌር ሪዘርቭ የተፈጥሮ የደን ሃብት በመካከሉ የጊሎና የአሌሮ ወንዞች አቋርጠውት ያልፋሉ፤ በሰሜና ምዕራብ አቅጣጫ ጠርዝ በባሮ ወንዝ፤ በምስራቅና በደቡብ አቅጣጫ ጠርዝ ደግሞ በአኮቦ ወንዝ ታቅፏል።

የተፈጥሮ የደን ሀብቱ ባለው ሜዳማና አረንጓዴያማ መልካ ምድራዊ ገጽታው በመሃሉና በጠርዞቹ ላይ የሚያልፉት ወንዞች ማራኪና ልዩ የውበት ገጽታዎችን አላብሰውታል። ጥብቅ የደን ሃብቱ ከጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ የብዝሃ ህይወት ሀብቱ ስብጥር ከፍተኛ ነው።

የደን ሃብቱ ውስጡ ከ1 ሺህ በላይ የዕጽዋት፣ 69 የአጥቢ እንሰሳት፣ 327 የአዕዋፋትና በተጠቀሱት ትላላቅ ወንዞች ከ113 በላይ የዓሳ ዝርያዎች ያሉት መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል።

በባዮስፌር ሪዘርቭነት የተመገቡት ጥብቅ የተፈጥሮ የደን ሃብቶች የአካባቢውን ስነ-ምህዳርና የአየር ንብረት ሚዛን በማስጠበቅ ረገድ የጎላ አበርክቶ አላቸው።


 

በባዮስፌር ሪዘርቭነት የተመዘገቡትን ሁለቱን ጥበቅ የተፈጥሮ ደን ሃብቶች ጨምሮ በርካታ የቱሪዝም መስህቦች በክልሉ እንደሚገኙ የገለጹት በክልሉ ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መስህቦች መዳረሻና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ደርባቸው ሸዋለም ናቸው።

በተለይም በተፈጥሮ የደን ሃብቶቹ ውስጥ የሚገኙት ፏፋቴዎች፣ ሐይቆች፣ ወንዞች፣ አጥቢ እንስሳቶች፣ የአዕዋፍ ዝርያዎችና ሌሎችም የብዝሃ ህይወት ሃብቶች ለቱሪዝም ኢንዲስትሪው ትልቅ አቅም መሆናቸውን አንስተዋል።


 

በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የደን ዘርፍ ባለሙያው አቶ ፓል ኛክ፤ በክልሉ የግብርና ልማትን በማሳለጥ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ መሰረት መኖሩን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች ያሉ እምቅ ሃብቶችን በተደመረ አቅም በአግባቡ በማልማት ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለ እድገትና ማንሰራራቷን እውን ማድረግ ይቻላል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም