ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን ተደራሽነት ለማስፋት እየተሰራ ነው - ኢንጂነር ጌቱ ገረመው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦በመላ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን ተደራሽነት ለማስፋት ተቋሙ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ በተለምዶ ሀጫሉ መንገድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያስገነባውን የኤሌክትሪክ ቻርጅ መሙያ ጣቢያ አስመርቋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ተቋሙ በአንድ ቀን 11 የቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን ማስመረቁ ለተቋሙ ልዩ ቀን ነው።

በሀጫሉ መንገድ የተገነባው የቻርጅ መሙያ ማዕከል ከከተማው አስተዳደር ጋር በትብብር የተሠራ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ ወደ 12 የሚጠጉ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ የማድረግ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።

ማዕከሉ በአካባቢው ያለውን የቻርጅ መሙያ አገልግሎት ፍላጎት እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ወደፊትም የማዕከሉን አቅም ለማስፋት ሰፊ ዕድል መኖሩን ጠቁመዋል።


 

በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን በስፋት ለማስገንባት ተቋሙ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣዩ አንድ ዓመት የቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን ቁጥር ከአሁኑ በአምስት ዕጥፍ ለማሳደግ ዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል።

ከአዲስ አበባና አካባቢዋ ባሻገር ድሬዳዋ፣ መቐለ፣ ባሕር ዳር፣ አርባ ምንጭና ሌሎች የክልል ከተሞችንም በተለያዩ የሥራ ምዕራፎች የቻርጅ መሙያ አገልግሎቱን ለማዳረስ መታቀዱን አስረድተዋል።

ተቋሙ የንጹሕ ኃይል አጠቃቀምን ለማስፋፋት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማበረታታትና የቻርጅ መሙያ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም