በዞኑ አርሶ አደሩ በቡናና ፍራፍሬ ልማት ዘላቂ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ አርሶ አደሩ በቡናና ፍራፍሬ ልማት ዘላቂ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው
ደብረ ማርቆስ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሩ ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን በቡናና ፍራፍሬ ልማት ዘላቂ ተጠቃሚነቱን የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ ሃብታሙ ማሕመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ አርሶ አደሩ ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን በቡናና ፍራፍሬ ልማት ዘላቂ ተጠቃሚነቱን የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ ነው።
በዚህም ለመስኖና ለመኸር ችግኝ ተከላ ከ5 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኝ ማዘጋጀት መቻሉን ጠቁመው፣ ከዚህ ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆነውን በመስኖ የመትከል ሥራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ከ50 ሺህ በላይ የፍራፍሬና የቡና ችግኝ በመስኖ ማልማት መቻሉን ጠቁመው፣ ዘንድሮ ይህንን በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ይህም አርሶ አደሩ ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን በቆላ ፍራፍሬ ልማት ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
በደብረ ኤሊያስ ወረዳ የገነቴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ያደለው ገዳሙ በበኩላቸው ቡና፣ አቮካዶና ማንጎ በክረምትና በበጋ በመትከል እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ደግሞ አቮካዶን በመስኖ ለማልማት ከሩብ ሄክታር በላይ መሬት ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በባሶ ሊበን ወረዳ የልምጭም ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ጌታቸው ቢሻው በበኩላቸው፤ በዚህ ዓመት ከ50 በላይ የፓፓያና የማንጎ ችግኝ በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቆላ ፍራፍሬ የተሸፈነ መሆኑንም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።