ቀጥታ፡

247ኛው የሚላን ደርቢ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ በጣልያን ሴሪአ የ10ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኤሲ ሚላን እና ኢንተር ሚላን የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ጨዋታው በሳንሲሮ ስታዲየም ምሽት 4 ሰዓት ከ45 ላይ ይካሄዳል።

ኤሲ ሚላን በውድድር ዓመቱ ዘጠኝ ጨዋታዎችን አከናውኖ በአምስቱ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።

18 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 11 ግቦች ተቆጥረውበታል። ሚላን በ18 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የከተማ ተቀናቃኙ ኢንተር ሚላን በሊጉ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መካከል ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል።

በጨዋታዎቹ ላይ 25 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ25 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የአሁኑ ለ247ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 246 ጨዋታዎች ኢንተር ሚላን 91 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ኤሲ ሚላን 84 ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪዎቹ 71 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

በሴሪአው 184 ጊዜ ተገናኝተው ኢንተር ሚላን 70፣ ኤሲ ሚላን 57 ጊዜ አሸንፈዋል። 57 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።

ባለፉት አምስት የሴሪአ ግንኙነታቸው ኤሴ ሚላን በሶስቱ ሲያሸንፍ ኢንተር አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

ባለፈው የውድድር ዓመት ያደረጓቸውን ሁለት የሴሪ አ ጨዋታዎች ኤሲ ሚላን በማሸነፍ ስድስት ነጥብ ወስዷል።

ክለቦቹ ለ118 ዓመታት የዘለቀ ተቀናቃኝነት አላቸው። ኢንተር ሚላን 21 እና ኤሲ ሚላን 19 ጊዜ የሴሪአ ዋንጫን አንስተዋል።

በአህጉራዊ መድረክም ኤሲ ሚላን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ሰባት ጊዜ በማንሳት ስኬታማው ክለብ ነው። ኢንተር ሚላን ሶስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።

ኢንተር ሚላን ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። በአንጻሩ ኤሲ ሚላን ድል ከቀናው ከከተማ ተቀናቃኙ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ዝቅ ያደርጋል።

የ45 ዓመቱ ማርኮ ጉይዳ ተጠባቂውን የደርቢ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም