የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለ በመሆኑ ተቀባይነቱ እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለ በመሆኑ ተቀባይነቱ እያደገ መጥቷል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በሰጥቶ መቀበልና በዓለም አቀፍ መርህ የተቃኘ በመሆኑ ተቀባይነቱ እያደገ መጥቷል ሲሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በሕግ፣ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ፍላጎት እና በመልከዓ ምድራዊ ቅርበት ላይ የተመሠረተ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ምሁራኑ ተናግረዋል።
ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ዮናስ ወልደየስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ፍላጎት የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት የሚጻረር ሳይሆን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የተከተለ ነው።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ፣ ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የነዳጅ ማውጫ እና የኢነርጂ ተቋማት መገንባትን ጨምሮ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን መጀመሯን አንስተዋል።
ይህም ተጨማሪ የባህር በር አማራጮችን ማግኘትን ሀገራዊ የህልውና እና የልማት ጥያቄ አድርጎታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጥያቄ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልከዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አመክንዮዎች ያሉት የማይቀለበስ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ግብጽ እና ሌሎች ሀገራት የዓባይ ወንዝን አጠቃቀም በተመለከተ ለትውልዶቻቸው በሚያስተምሩበት አግባብ ኢትዮጵያውያንም በባህር በር እና በውሃ ሀብታቸው ዙሪያ በሳይንሳዊ ማስረጃ የተደገፈ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መሥራት ከእኛ ይጠበቃል ብለዋል።
ግብጽ የኢትዮጵያን ሕጋዊ መሠረት ያለው ጥያቄ በማዛባት ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ጭምር ለማሳሳት ሙከራ ማድረጓን ቀጥላለች ያሉት አቶ ዮናስ፤ መሰል እንቅስቃሴዎችን የመመከቱ ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት መምህርና ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሌሎች ሀገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ማይሎችን አቋርጠው ቀይ ባህር ላይ ጥቅማቸውን እያስከበሩ፣ ከቀይ ባህር 60 ኪሎ ሜትር ብቻ የምትርቀው ኢትዮጵያ ከባህር እንድትርቅ መደረጉ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
በቀይ ባህር ላይ ጥቅሞቿን ማስከበር የኢትዮጵያ የማይቀለበስ መብቷ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በሰጥቶ መቀበልና ዓለም አቀፍ መርህ የተቃኘ በመሆኑ ተቀባይነቱ እያደገ መጥቷል ያሉት ተመራማሪው፤ በብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ በጋራ ከቆምን የማይሳካበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።
የቀይ ባህርና የኤደን ባህረ ሰላጤ መርከቦችን የሚያግቱ እና የወንጀል ድርጊቶችን የሚፈጽሙ የባህር ላይ ወንበዴዎች የሚስተዋሉበት ቀጣና መሆኑን አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር መመለስ ለቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወትም ጠቁመዋል።
ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ከማሳለጥ አኳያም የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር መመለስ ዘርፈ ብዙ ቀጣናዊ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።