ቀጥታ፡

በሊበን ወረዳ ከ15 ሺህ የሚበልጡ የአርብቶ አደር ልጆች የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል

ነገሌ ቦረና  ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ በደቡብ ኦሮሚያ ዞን ሊበን ወረዳ ከ15 ሺህ የሚበልጡ የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ልጆች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ መሆናቸውን የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የሊበን ወረዳ በአብዛኛው ቆላማ፣ ለዝናብ አጠርና ለድርቅ ተጋላጭ በመሆኑ የወረዳው አርብቶ አደር ማኅበረሰብ በእንስሳት እርባታ የሚተዳደር ነው።

የክልሉ መንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ከሰጣቸው ቆላማ ወረዳዎች መካከልም አንዱ ነው።


 

የሊበን ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት የምገባ ሥርዓተ ትምህርት ባለሙያ ወይዘሪት ቃሊቲ አባዱባ ለኢዜአ እንዳሉት፡ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ18 ሺህ በላይ ሕጻናትን በምገባ መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።

በምገባ መርሃ ግብሩ በወረዳው የሚገኙ 105 አንደኛና ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መለየታቸውን አስታውቀዋል።

እስካሁን በወረዳው ሁሉም ቆላማ ቀበሌዎች ከ15 ሺህ 400 በላይ ሕጻናት የምገባ መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ በመሆን ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ከመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች መካከል 2 ሺህ 500 የሚሆኑት የቅድመ መደበኛ ተማሪ ሕጻናት ሲሆኑ ቀሪዎቹ የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለመርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ እስካሁን ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው 515 ኩንታል የምግብ እህል መቅረቡን ገልጸዋል።

ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነት በቡሳ ጎኖፋ አማካኝነት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

መርሃ ግብሩ የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ ከመቀነስ ባለፈ ለአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ እፎይታን ማምጣቱን አውስተዋል።


 

በሊበን ወረዳ የቡርሪ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አደም አብዲ፣ መርሃ ግብሩ የልጆችን ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ ፍላጎት ከማዳበሩ ባለፈ ጠንክረው እንዲማሩ ማድረጉን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲዘልቅ ኃላፊነት ስላለብን ያልተቋረጠ ድጋፍና ትብብር እናደርጋለን ብለዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ማሙሽ ግርማ ለትምህርት ጥራትም ሆነ ተደራሽነት መርሃ ግብሩ አስፈላጊ መሆኑን አመላክቷል።


 

ከድርቅና ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ በቆላማ አካባቢዎች ሕጻናት ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ እንደሚያጋጥም አስታውሷል።

መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ ሕጻናት ትምህርት ከማቋረጥ ይልቅ በአግባቡ እየተማሩ መሆናቸውን አስረድቷል።

በወረዳው በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ20 ሺህ በላይ ሕጻናት በመደበኛ ትምህርት ፕሮግራም ተመዝግበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም