ለተኪ ምርትና ወጭ ንግድ የተሰጠው ትኩረት ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
ለተኪ ምርትና ወጭ ንግድ የተሰጠው ትኩረት ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን አሳድጓል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ)፦ በመደመር መንግሥት ለተኪ ምርትና ወጭ ንግድ የተሰጠው ትኩረት ምርትና ምርታማነትን ከማሳደጉም ባሻገር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንዲያድግ ማስቻሉን አምራቾች ገለጹ።
በኢንዱስትሪ ዘርፍ የነበሩ ማነቆዎችን ለማሻሻል ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምና ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተተግብረዋል።
በዚህም ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሀገሪቱን የንግድ ሚዛን መዛባት በዘላቂነት ለማስተካከል መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ በተለይ በአምራች ዘርፉ የነበሩ ማነቆዎችን በመፍታት ተኪ ምርትና የወጪ ንግድ እንዲያድግ እያስቻለ ይገኛል።
የስርጉ ኑሪ ኢብራሂም ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ ሙራድ በድሩ እንዳሉት፤ ድርጅቱ በስሩ ባሉት አልፋ ፉድስ ኮምፕሌክስና ኦሜጋ ኢምፖርት ኤክስፖርት ድርጅቶች ተኪ ምርትና የወጭ ንግድ ላይ ተሰማርቷል።
ድርጅቱ በምግብ ማቀነባበርና በላኪና አስመጪነት የተሰማራ ሲሆን ለ800 ቋሚና ከ100 በላይ ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሯል።
የመደመር መንግሥት ለአምራች ዘርፉ ትኩረት በመስጠት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም መደረጉ ለዘርፉ እድገት አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል።
ድርጅቱ ስጋ ወደውጭ እንደሚልክ ተናግረው የተደረጉ ማሻሻያዎች የስጋ ወጭ ንግድ እንዲያድግ ማስቻሉን ተናግረዋል።
የኒውዊንግ አዲስ ጫማ ፋብሪካ የሰው ኃይል ስራ አስኪያጅ ብዙአየሁ ወርቁ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎችና ለአውሮፓና አሜሪካ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአምራች ዘርፉ የተሰጠው ትኩረትና የተደረጉ ማሻሻያዎች ከዚህ ቀደም ይገጥም የነበረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር እንዲፈታ ማስቻሉንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት መተግበሯም የበለጠ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ እንደሆነም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማህበር ቦርድ ፕሬዝዳንት ከሊፋ ሁሴን፤ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተደረጉ ማሻሻያዎች ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እያስቻሉ መሆኑን ተናግረዋል።
የተደረጉ ማሻሻያዎች በዘርፉ ለነበሩ ችግሮች መፍትሄ በማበጀት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እያሳደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ለአምራች ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የሀገር ውስጥ አምራቾች በገበያ ላይ ያላቸው የምርት ድርሻ ወደ 45 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ የፋብሪካዎች አማካይ የማምረት አቅምም ከነበረበት 47 በመቶ ወደ ከ69 በመቶ በላይ ከፍ ብሏል።
የማምረቻው ዘርፍ እድገት በ2013 ዓ.ም 4 ነጥብ 8 ከነበረው በ2018 ዓ.ም 15 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን አንስተው ይህንን እድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።