ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በሌማት ትሩፋት በሚከናወኑ ስራዎች በሩብ ዓመቱ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል

‎ባህርዳር ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት በሌማት ትሩፋት ስራዎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከዕቅድ በላይ የእንቁላል ምርት ለገበያ መቅረቡን ገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋ ይስማው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የከተማና የገጠሩን ማኅበረሰብ ምርታማነት በማሳደግ ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ከ26 ሚሊዮን በላይ የአንድ ቀን ጫጩቶችን ለአሳዳጊዎች ለማቅረብ ታቅዶ በተደረገ ጥረት በሦስት ወራት ብቻ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ማሰራጨት መቻሉን ገልጸዋል።


 

ጫጩቶቹን ማሰራጨት የተቻለውም ለ2 ሺህ 567 አሳዳጊዎች መሆኑን ጠቁመው የተገኙትም ከኢትዮ-ችክን፣ ከአንዳሳ፣ ከዳባትና ከኮምቦልቻ የዶሮ ብዜት ማዕከላት መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በሩብ ዓመቱ 480 ሚሊዮን የእንቁላል ምርት ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ በተሰራው ሥራ ከዕቅድ በላይ ምርት ቀርቦ ለተጠቃሚዎች መሰራጨቱን አስረድተዋል።

ለዶሮና እንቁላል ምርትና ተጠቃሚነት የተሰጠውን ትኩረት ለማስቀጠል በሰቆጣ ከተማ ለተገነባው የጫጩት ማስፈልፈያ ማዕከል ማሽኖች ተሟልተው እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።

በጎንደር ከተማ ለሚገነባው የዶሮ ጫጩት ማስፈልፈያ ቦታ በመረከብ ግንባታውን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተያዙ ግቦችን በማሳካት የሥርዓተ ምግብ ችግርን ለማሻሻልና ገበያን ለማረጋጋት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የደሴ ከተማ ነዋሪው ወጣት አስናቀ ክንዴ፣ አምስት ሆነው በመደራጀት ባገኙት የመስሪያ ሼድ 550 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በመግዛት የእንቁላል ምርት ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ገልጿል።


 

በቀን ከ430 በላይ እንቁላል በመሰብሰብ ለአካባቢው ነዋሪዎችና ነጋዴዎች እያቀረቡ መሆኑን ጠቁሞ፣ በ100 ሺህ ብር ካፒታል የጀመሩት ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ600 ሺህ ብር በላይ መድረስ መቻሉን አስረድቷል።

የአንድ ቀን ጫጩት ተረክበው በማሳደግ ለተለያዩ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ለሌሎች አርቢዎች በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን የገለጸው ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ወጣት መሀመድ ሰይድ ነው።


 

በአሁኑ ወቅትም እያሳደጓቸው የሚገኙ ከ1 ሺህ 500 በላይ የ45 ቀን ዶሮዎችን ለመሸጥ ገበያ እያፈላለጉ መሆኑንም ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም