የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለመገንባት እንችል ዘንድ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ አለብን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለመገንባት እንችል ዘንድ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ አለብን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለመገንባት እንችል ዘንድ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የመደመር መንግሥት አመራሮች በሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ሥልጠና በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለመገንባት እንችል ዘንድ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።
ሁለንተናዊ ብልጽግና ማለት ቁሳዊና መንፈሳዊ ብልጽግና፣ ባህላዊና ሞራላዊ ብልጽግና የተሸመኑበት ብልጽግና ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ደግሞ አመራሩ ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያስፈልገዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በአካል የዳበረ፣ በሞራል የጠነከረ፣ በዕውቀት የተሳለ፣ በጥበብ የበሰለ እንዲሆን እንደሚጠበቅበት ገልጸው በተለይም በሀገር ፍቅር ስሜትና በሕዝብ ተቆርቋሪነት መንፈስ ግዴታዎቹን እንዲወጣ የሀገር አደራዋ ጥብቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
ወታደራዊ ሳይንስ፣ ልምድ እና ሕይወት የሰውን ልጅ ዓላማና ሰብእና በመቅረጽ ረገድ ተወዳዳሪ የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰው ልጅ በአካልም፣ በመንፈስም፣ በሥነ ምግባርም፣ በአፈጻጸምም ዲሲፕሊናዊ እንዲሆን በማስቻል ለዘመናት ትውልድን ሲያዘጋጅ ኖሯል ብለዋል።
ውጫዊና ውስጣዊ ማንነቱ የሠመሩለት ሰብእና በመቅረጽም ታላላቅ መሪዎችን አፍርቷል ብለዋል፡፡
ግዳጅን በብቃት መፈጸም፣ በዐርበኝነት መንፈስ አገልግሎት መስጠት፤ የሥራ ዲሲፕሊንን መቅረጽ፤ የጋራ ግብን በጋራ ማሳካት፤ ወትሮ ዝግጁነት፤ በተዋረድ አመራርን ማፍራት፤ ኃላፊነትና ተጠያቂነት፤ ከላይ እስከ ታች በመናበብ ዓላማን መፈጸም፣ እና የመሳሰሉት ከወታደራዊ ሳይንስና ልምድ ሊወሰዱ የሚችሉ ዕሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡
የመደመር ሥልጣኔ ታላቁ ስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል፣ ከወታደራዊ ሳይንስና ሕይወት የምንቀስማቸው ዕውቀቶች፣ ክሂሎቶች እና ልምዶች አሉን ሲሉም ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ በአንድ ሰዋሰው መግባባት፣ ሥነ ምኅዳርን በሚገባ መጠቀም፤ በተከታታይ ሕዝብን ለዓላማና ለተግባር ማነጽ፤ ለሕዝብ የገባነውን ቃል በሚገባ አከናውኖ መጨረስ፤ ከታች እስከ ላይ ያለውን መዋቅር ለሀገራዊ ዓላማ ማሣለጥ፤ ሀገርን በባለ አደራነት መምራት፤ ለምንምና ለማንም የማትበገር ጽኑ ሀገር መገንባት፤ ተተኪ ትውልድን ማፍራት እና የሀገርን ደኅንነት ምንጊዜም ማረጋገጥ የሚሉትን የስትራቴጂውን ሐሳቦች በተገቢው መንገድ ለመረዳትም ሆነ ለማስፈጸም ወታደራዊ ሥልጠናው የማይናቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
ወታደሮች ዒላማ፤ ሲቪሎች ደግሞ ዓላማ አላቸው፡፡ የሁለቱም ግብ ድልን ማስመዝገብ ነው፡፡ ሁለቱን ዲሲፕሊኖች በማገናዘብ ዒላማውንም የሚመታ፤ ዓላማውንም የሚያሳካ ትውልድ እንፈጥራለን ብለዋል፡፡