ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የጤና ምርቶች ማምረቻ ማዕከል እየሆነች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የጤና ምርቶች ማምረቻ ማዕከል እየሆነች መምጣቷን “ሄልዝ ፎር ዲቭሎፕመንት” የተሰኘ ተቋም መስራች ዶክተር ኢያን ባርተን ገለጹ።

ዶክተር ኢያን ባርተን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የወሰደቻቸው ጠንካራ የፖሊሲ እርምጃዎች፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን ማሻሻሏ እና ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር መፍጠሯ ተፈላጊነቷን መጨመሩን አመልክተዋል።

የተደረጉት ማሻሻያዎች በመድኃኒት አምራችነት እንዲሁም በጤና ምርቶችና ግብአቶች ዘርፍ ውስጥ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አዳዲስና ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎችን እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የመድኃኒት ዘርፍ ውስጥ ለሁለት አስርታት ዓመታት ገደማ የሠሩት ዶክተር ባርተን፣ ሀገሪቱ ቀደም ሲል በንግድ ገደቦች እና በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ምርትና አገልግሎት ለማቅረብ ፈታኝ ከነበሩ ገበያዎች አንዷ እንደነበረች አውስተዋል።

ይሁንና መንግስት ባለፉት ዓመታት ያደረጋቸው ሪፎርሞች በጤናው ዘርፍ ምቹ ምህዳር መፍጠራቸውን ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ የምሥራቋ ጌጥ ናት ያሉት ዶክተር ባርተን ሀገሪቷ አስደማሚ ኢኮኖሚና ሕዝብ ያላት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

ይህን ታላቅ ለውጥ እያመጡ ያሉት በመንግሥት የተወሰዱ የፖሊሲ ማሻሻያዎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ የለውጡ በጎ ተፅዕኖ ከጤና ምርቶች ማኑፋክቸሪንግ አልፎ ወደ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችም መስፋት እንደሚችልም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እና ያላት የኢኮኖሚ አቅም፣ በአፍሪካ አህጉር ላይ ስራቸውን ለማስፋት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ትልቅ እድል መሆኑን አንስተዋል።

በማንኛውም ኩባንያ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ውስጥ ኢትዮጵያ ማዕከል ልትሆን እንደሚገባ አንስተዋል።

አፍሪካ መድኃኒቶችን፣ ክትባቶችን እና የሕክምና መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅሟን ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት እውን ለማድረግ ኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደምትችል ገልጸዋል።

የአፍሪካን ሀገር በቀል የማኑፋክቸሪንግ አቅም ማሳደግ ለአህጉሪቷ ነጻነትን የሚያመጣ መንገድ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በአፍሪካ በጤናው ዘርፍ እየታየ ያለው እድገት ዘላቂ እንዲሆን መንግሥታት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በምርምርና ልማት፣ በፈጠራ ማዕከላት እና ሀገር በቀል ክህሎትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ኢንቨስትመንቶች እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም