ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ)፦‎ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 10 ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመቻል በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድሬዳዋ ከተማን 1 ለ 0 ሲረታ መቻል በቦሌ ክፍለ ከተማ የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል።

ጨዋታው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ መቻል የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት የሚያደርጉት ነው።

ሁለቱ ክለቦች በ2018 ዓ.ም የውድድር ዓመት በሊጉ እርስ በእርስ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንዱ ድል ሲቀናው በቀሪው መርሐ ግብር አቻ ተለያይተዋል።

ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላኛው ሸገር ከተማ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 8 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአንደኛ ሳምንት ጨዋታ ሸገር ከተማ ከአዲስ አዳጊው ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ጋር ሶስት አቻ ተለያይቷል።

አዳማ ከተማ ከልደታ ክፍለ ከተማ ያደረገው ጨዋታ ያለ ግብ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ቡድኖቹ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።

ይርጋጨፌ ቡና ከሀዋሳ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ይካሄዳል።

በመጀመሪያ ሳምንት ይርጋጨፌ ቡና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2 ለ 1 ሽንፈት ሲያስተናግድ ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ባህር ዳር ከተማን 2 ለ 1 ረትቷል።

ይርጋጨፌ ቡና የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት፣ ሀዋሳ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማሉ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት እስከ ነገ ይቆያል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሶስት ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል። 

እጸገነት ግርማ (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ)፣ ማርታ ወልዴ (ሸገር ከተማ) እና ፍጹም ፈለሃ (ጉለሌ ክፍለ ከተማ) በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን በማግባት የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ እየመሩ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም