ቀጥታ፡

ባየር ሙኒክ እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ የሚያደርጉት ተጠባቂ የደርቢ ጨዋታ   

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2019(ኢዜአ):- በጀርመን ቡንድስሊጋ የስምንት ሳምንት መርሃ ግብር ባየር ሙኒክ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
 
ጨዋታው ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ 75 ሺህ 024 ተመልካች በሚያስተናገደው አሊያንዝ አሬና ስታዲየም ይደረጋል።
 
ባየር ሙኒክ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች አምስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ወጥቷል። ቡድኑ 25 ግቦችን ሲያስቆጥር ስድስት ጎሎችን አስተናግዷል።
 
ሙኒክ ሊጉን በ17 ነጥብ እየመራ ይገኛል።
 
ተጋጣሚው ቦሩሲያ ዶርትሙንድ  ስድስት ጨዋታዎችን አከናውኖ አምስት ጊዜ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ  ነጥብ ተጋርቷል። ቡድኑ 12 ግቦችን ሲያስቆጥር 4 ግቦችን አስተናግዷል።
 
ዶርትሙንድ በተመሳሳይ 17 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
 
ሁለቱ የጀርመን ተቀናቃኝ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የአሁኑ ለ141ኛ ጊዜ ነው።
 
ባየር ሙኒክ 72 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ቦሩሲያ ዶርትሙንድ 35 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪው 33 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
 
ቡድኖቹ በቡንድስሊጋው 114 ጊዜ ተገናኝተው  ባየር ሙኒክ 55 ጊዜ ሲያሸንፍ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ 26 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 33 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

ባለፈው የውድድር ዓመት በቡንድስሊጋው ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች ባየር ሙኒክ በድል ተወጥቷል።

“ዴር ክላሲከር” የሚል ስያሜ ያለው የደርቢ ጨዋታ 61 ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።
 
በመልካም ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
 
የ45 ዓመቱ ቶቢያስ ስቲለር ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም