ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ይውላሉ።

በዕለቱ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከመርሐ ግብሮቹ መካከል ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታ ይገኝበታል።

ኢትዮጵያ ቡና በሶስት ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። ቡናማዎቹ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደዋል።

ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በአምስት ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ከድል ርቋል።

ሁለቱ ክለቦች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ትኩረት ስቧል።

ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላኛው የዕለቱ መርሐ ግብር ነው።

ከሶስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ ያገኘው ፋሲል ከነማ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ባህር ዳር ከተማ በስድስት ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።

በአራተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ፋሲል ከነማ በሀዲያ ሆሳዕና የ1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።

ባህር ዳር ከተማ በአራተኛ ሳምንት ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ በአህጉራዊ ጨዋታ ምክንያት መራዘሙ የሚታወስ ነው።

ቡድኑ በሶስተኛ ሳምንት ጨዋታው ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 አሸንፏል።

ጨዋታው ፋሲል ከነማ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት፣ ባህር ዳር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው።

ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ አንድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አላቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም