የመንግሥትን የልማት ጥረትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን- የደቡባዊ ሲዳማ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥትን የልማት ጥረትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን- የደቡባዊ ሲዳማ ዞን ነዋሪዎች
አለታ ወንዶ፣ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ )፡-የመደመር መንግሥትን የልማት ጥረትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በሲዳማ ክልል የደቡባዊ ሲዳማ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ ።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ኃይሉ ( ዶ/ር ) በመደመር መንግሥት የተያዙ የልማት ዕቅዶችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ከደቡባዊ ሲዳማ ዞን ነዋሪዎች ጋር በአለታ ወንዶ ከተማ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ሌሎችም ጉዳዮችን በማንሳት የመንግስት ጥረት እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በሁሉም ረገድ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥረቶች መልካም መሆናቸውን አንስተው፤ በዚህ ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ቦጋለ አዳሙ፤ በከተማና በገጠር ልማት፣ በግብርና ልማትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ተስፋ የሰነቅንባቸው ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም የልማት ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለሙሆኑና የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑን በማንሳት ለላቀ ስኬት እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ አማረች እንዳለለት እና አቶ ተስፋየ ቡርቃ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠልና ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ማከናወን ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በተለይም ከመሰረተ ልማት ግንባታ ጋር በተያያዘ ይነሱ የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት የመንግሥት ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተው የተጀመሩ ስራዎችን ለማሳለጥ የሁላችንም ተሳትፎ፣ ትብብርና እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል።
በመሆኑም የመደመር መንግሥትን የልማት ጥረትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ኃይሉ ( ዶ/ር)፤ የመደመር መንግሥት የህዝብን የልማት ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ ለጋራ ተጠቃሚነት፣ ለሀገር እድገትና ማንሰራራት በትጋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ባለፉት ጥቂት አመታት የተመዘገቡ ስኬቶችንና ተጨባጭ ውጤቶችን ጠቅሰው ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመሆኑም በመንግሥት የተያዙ የልማት እቅዶች እንዲሳኩ የህዝቡ ድጋፍ፣ ተሳትፎና እገዛ ወሳኝ መሆኑን አንስተው አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነት የማሳደግ ብሎም የሥራ ዕድል ፈጠራን በማስፋት ከድህነት የመውጣት ጥረታችን ይቀጥላል ብለዋል።
የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።